ጻድቃን ሲሞቱ ማንም ትኲረት አይሰጠውም፤ ደጋግ ሰዎች በሞት ሲወሰዱ ከክፉ ነገር እንዲድኑ የተወሰዱ መሆናቸውን ማንም ሰው ሊያስተውለው አይችልም። ቀጥተኛ ሕይወትን የሚኖሩ ሰዎች ሰላም ይኖራቸዋል፤ በሚሞቱበትም ጊዜ ዕረፍትን ያገኛሉ። ከአስማተኞች፥ ከአመንዝራዎችና ከዘማውያን የማትሻሉ እናንተ ወደ እዚህ ቅረቡ! እናንተ የምታፌዙ፥ አፋችሁን የምትከፍቱትና ምላሳችሁን የምታወጡት በማን ላይ ነው? እናንተ ዐመፀኞችና ሐሰተኞች ልጆች አይደላችሁምን? እናንተ በዋርካ ዛፎች መካከልና በየለምለሙ ዛፍ ሥር በፍትወት የምትቃጠሉ ናችሁ፤ እንዲሁም በሸለቆዎች ውስጥ በቋጥኞች መካከል ልጆቻችሁን ለዕርድ ታቀርባላችሁ። ከሸለቆ ለስላሳ ድንጋዮች መካከል መርጣችሁ አማልክታችን ናቸው በማለት የመጠጥና የእህል ቊርባን ታቀርቡላቸዋላችሁ። በዚህ ነገር አልቈጣምን? በከፍተኛ ተራራ ጫፍ ላይ ዝሙት ለመፈጸምና መሥዋዕት ለማቅረብ ትወጣላችሁ። ከበራችሁና ከመቃኖቹ በስተጀርባ የጣዖት ምስሎችን አስቀምጣችኋል፤ እኔን ትታችሁ ዝሙት ለመፈጸም ወደ አልጋዎቻችሁ ወጥታችኋል፤ በዝሙት ዋጋ ተደራድራችሁ ፍትወታችሁን ታረካላችሁ። ብዙ ዘይትና ሽቶ ተቀብታችሁ ሞሌክ ወደ ተባለው ጣዖት ሄዳችሁ፤ የምታመልኳቸውን ጣዖቶች ለመፈለግ መልእክተኞቻችሁን ወደ ሩቅ ቦታ ወደ ሙታን ዓለም እንኳ ሳይቀር ላካችሁ። ከብዙ መንከራተታችሁ የተነሣ ትደክማላችሁ፤ ሆኖም ግን ፍላጎታችሁ በጣም ስለ ተነሣሣ “ጠቃሚ አይደለም” ብላችሁ አላቆማችሁም። “እኔን ባለማስታወስና ስለ እኔ ባለማሰብ ውሸት የተናገራችሁት ማንን ፈርታችሁ ነው? እኔን ያልፈራችሁኝ ለብዙ ጊዜ ዝም ስለልኩና እንዳላየ ስለሆንኩ ነውን? ትክክል ናቸው ብላችሁ የምታስቡአቸውን ሥራዎቻችሁን አጋልጣለሁ፤ ጣዖቶቻችሁም ሊረዱአችሁ አይችሉም። ርዳታ ለማግኘት በምትጮኹበት ጊዜ እስቲ የሰበሰባችኋቸው ጣዖቶቻችሁ ያድኑአችሁ! እነርሱን የነፋስ ሽውታ ያስወግዳቸዋል፤ እስትንፋስም ይወስዳቸዋል፤ በእኔ የሚተማመን ግን ምድሪቱ የእርሱ ትሆናለች፤ የተቀደሰ ተራራዬንም ርስት ያደርጋል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “አስተካክሉ፥ አስተካክሉ፥ መንገዱን ጥረጉ! ሕዝቤ ከሚሄዱበት መንገድ መሰናክሉን አስወግዱ!” ከፍተኛውና ከሁሉ የላቀው፥ ለዘለዓለም የሚኖር ቅዱሱ እንዲህ ይላል፦ “እኔ በተቀደሰና በከፍተኛ ቦታ፥ እንዲሁም ልባቸው ከተሰበረና መንፈሳቸው ትሑት ከሆኑት ጋር እኖራለሁ፤ ይኸውም ትሑት መንፈሳቸውንና የተሰበረ ልባቸውን ለማደስ ነው። እኔ ዘወትር ሰውን አልወቅስም፤ ሁልጊዜም አልቈጣም፤ ይህን ባደርግ ኖሮ፥ የፈጠርኳቸው ሰዎች መንፈሳቸው ይዝል ነበር። ክፉ በሆነው ስግብግብነታቸው ምክንያት በእነርሱ ላይ ተቈጥቼ ነበር፤ እንዲሁም እነርሱን ቀጥቼ ተለይቼአቸው ነበር፤ እነርሱም ወደ ራሳቸው መንገድ ተመለሱ። “እኔ ሥራቸውን ሁሉ ተመልክቼአለሁ፤ ይሁን እንጂ እፈውሳቸዋለሁ፤ እመራቸዋለሁ፤ እኔ ለእነርሱና ስለ እነርሱ ለሚያለቅሱት ሙሉ መጽናናትን እሰጣለሁ። በሩቅና በቅርብ ላሉትም ሁሉ ሰላም ይሁን! እኔ ሕዝቤን እፈውሳለሁ፤ ክፉ ሰዎች ግን እንደሚናወጥ ባሕር ናቸው፤ ውሃውም ቈሻሻውንና ጭቃውን ቀስቅሶ ያወጣል እንጂ ጸጥ አይልም። ለክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል አምላኬ።
ትንቢተ ኢሳይያስ 57 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 57:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች