የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 54

54
እግዚአብሔር ለእስራኤል ያለው ፍቅር
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ባል ካላት ሴት ይልቅ ፈት የሆነችው ልጆች ብዛት ያላቸው ስለ ሆነ፥
ልጅ እንዳልወለደችና አምጣ እንደማታውቀው ሴት የሆንሽው ኢየሩሳሌም ሆይ!
እልል እያልሽ ዘምሪ! #ገላ. 4፥27።
2የምትኖሪበትን የድንኳንሽንም ቦታ አስፊ፤
መጋረጃዎችሽም እንዲዘረጉ አድርጊ፤ አታጥብቢ፤
አውታሮችሽን አስረዝሚ፤
ካስማዎችሽንም አጠንክሪ።
3በሁሉም አቅጣጫ ድንበርሽን ታሰፊያለሽ፤
ዘሮችሽ አሕዛብ የያዙትን ቦታ ያስለቅቃሉ፤
በተለቀቁትም ከተሞች ይሰፍራሉ።
4ኀፍረትም ሆነ ውርደት ስለማይደርስብሽ አትፍሪ፤
በወጣትነትሽ ጊዜ የደረሰብሽን ኀፍረት ትረሺአለሽ፤
ባልዋ እንደ ሞተባት ሴት ብቸኛ ሆነሽ ያሳለፍሽውን የስድብ ዘመን አታስታውሺም።
5ይህም የሚሆነው ፈጣሪሽ የሠራዊት አምላክ
እግዚአብሔር እንደ ባልሽ ስለሚሆንና ‘የምድር ሁሉ አምላክ’
ተብሎ የሚጠራው የእስራኤል ቅዱስ አዳኝሽ ስለ ሆነ ነው።
6አንቺ በወጣትነት ዕድሜዋ አግብታ በመባረርዋ
ልብዋ እንደ ተሰበረ ሴት ነሽ፤”
ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክሽ እንደገና ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ ይልሻል፦
7ለጥቂት ጊዜ ብቻ ትቼሽ ነበር፤
ነገር ግን በታላቅ ርኅራኄ እመልስሻለሁ።
8እጅግ ከመቈጣቴ የተነሣ ለጥቂት ጊዜ ትቼሽ ነበር፤
ነገር ግን በዘለዓለማዊ ፍቅሬ እራራልሻለሁ፤
ይላል አዳኝሽ እግዚአብሔር።
9“በኖኅ ዘመን ‘ምድርን በውሃ መጥለቅለቅ
እንደገና አላጠፋትም’ ብዬ ቃል እንደ ገባሁ
እነሆ አሁንም ‘በአንቺ ላይ እንደገና
አልቈጣም’ ብዬ ቃል እገባልሻለሁ፤
ከእንግዲህም ወዲህ ተግሣጽ አላደርስብሽም። #ዘፍ. 9፥8-17።
10ተራራዎችና ኰረብቶች ሊናወጡና ሊፈርሱ ይችላሉ፤
እኔ ለአንቺ ያለኝ ፍቅር ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤
የሰላምንም የተስፋ ቃሌን ለዘለዓለም እጠብቅልሻለሁ፤”
ይላል ለአንቺ የሚራራ እግዚአብሔር።
አዲሲትዋ ኢየሩሳሌም
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“አንቺ የተሠቃየሽ፥ በዐውሎ ነፋስም የተዋከብሽና
ያልተጽናናሽ የኢየሩሳሌም ከተማ!
እኔ በከበረ ድንጋይ እሠራሻለሁ፤
መሠረትሽንም የምጥለው በሰንፔር ድንጋይ ነው። #ራዕ. 21፥18-21።
12የግንቦችሽን ጒልላት በቀይ መረግድ፥
የቅጽር በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቊ፥
በዙሪያሽ ያለውንም ቅጽር በከበሩ ድንጋዮች አንጻለሁ።
13“ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤
የልጆችሽም ሰላም የተሟላ ይሆናል። #ዮሐ. 6፥45።
14በፍትሕና በእውነት ላይ ትመሠረቺአለሽ፤
ግፍና ጭቈና ከአንቺ ይርቃል
የሚያስፈራሽም የለም፤ ሽብርም ከአንቺ ይርቃል፤
ወደ አንቺም አይቀርብም።
15በአንቺ ላይ አደጋ ለማድረስ የተነሡ ቢኖሩ
ከእኔ የተላኩ ስላልሆኑ ይወድቃሉ።
16“እነሆ፥ በወናፉ ፍሙን የሚያናፋውን ብረት
አቅላጭ የፈጠርኩ እኔ ነኝ፤
እርሱም መሣሪያውን የሚሠራው ለየተሠራለት
ዓላማ እንዲውል ለማድረግ ነው፤
ያጠፋ ዘንድ አጥፊውን የፈጠርኩ እኔ ነኝ።
17አንቺን ለማጥፋት የሚሠራ መሣሪያ ዘላቂነት አይኖረውም፤
ለሚከሱሽ ሁሉ በቂ መልስ ይኖርሻል፤
የእኔ አገልጋዮች ርስትና ከእኔ
የሚፈረድላቸው ፍርድ ይህ ነው፤” ይላል እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ