ትንቢተ ኢሳይያስ 53
53
የእግዚአብሔር አገልጋይ ለሰው ልጆች የዋለው ውለታ
1ሕዝቡም እንዲህ ሲሉ ይመልሳሉ፦
“እኛ የምንናገረውን ማን ያምነናል?
የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ? #ዮሐ. 12፥38፤ ሮም 10፥16።
2አገልጋዬ በደረቅ ምድር ላይ እንደሚወጣ ሥርና
እንደ ቡቃያ አድጓል፤
እንመለከተው ዘንድ ውበት ወይም ግርማ የለውም፤
እርሱን እንወደው ዘንድ ከመልኩ
አንዳች እንኳ የሚስብ ደም ግባት የለውም።
3እርሱም በሌሎች የተናቀና የተጠላ ነበር፤
እርሱ የመከራና የሐዘን ሰው ነበር።
ሰዎች ፊታቸውን እስኪያዞሩበት ድረስ
እርሱ የተናቀ፥ እኛም ያላከበርነው ሰው ነበር።
4“በእውነት እርሱ ደዌአችንን ተቀበለ፤
ሕማማችንንም ተሸከመ፤
እኛ ግን በእግዚአብሔር ተመትቶ እንደ ወደቀና እንደ ቈሰለ አድርገን ቈጠርነው። #ማቴ. 8፥17።
5እርሱ ግን ተወግቶ የቈሰለው ስለ መተላለፋችን ነው፤
የደቀቀውም ስለ በደላችን ነው፤
እኛ የዳንነው እርሱ በተቀበለው ቅጣት ነው፤
በእርሱም ቊስል እኛ ተፈወስን። #1ጴጥ. 2፥24።
6ሁላችንም እንደ በጎች ባዝነን ነበር፤
ሁላችንም ወደ ራሳችን መንገድ ሄደን ነበር፤
ነገር ግን እግዚአብሔር የሁላችንንም በደል በእርሱ ላይ አኖረ። #1ጴጥ. 2፥25።
7“እርሱ ግፍና ችግር ደረሰበት፤
ይሁን እንጂ ምንም አልተናገረም፤
ለመታረድ እንደሚወሰድ ጠቦትና
በሸላቾቹ ፊት ጸጥ እንደሚል በግ
ዝም አለ እንጂ ምንም አልተናገረም። #ራዕ. 5፥6።
8በእርሱ ላይ የተዛባ ፍርድ ተወስኖበት ተወሰደ፤
የወደፊትስ ሁኔታውን ማስተዋል የሚችል ማነው?
ሆኖም ስለ ሕዝቤ መተላለፍ ተመታ፤
ከሕያዋንም ዓለም ተወገደ። #ሐ.ሥ. 8፥32-33።
9ምንም ዐመፅ ሳይፈጽም፥
በአንደበቱም ሐሰት ሳይገኝበት፥
በሞቱ ከክፉ አድራጊዎች ጋር ተቈጠረ፤
በባለጸጋም መቃብር ተቀበረ።” #1ጴጥ. 2፥22።
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ይሁን እንጂ በሕማም አደቀው ዘንድ የእኔ ፈቃድ ነበር፤
ሕይወቱን የበደል መሥዋዕት አድርጎ
በሚያቀርብበት ጊዜ ዘመኑ ተራዝሞ ብዙ ትውልድ ያያል፤
በእርሱም አማካይነት የእኔ ፈቃድ ይፈጸማል።
11ጻድቁ አገልጋዬ ከሥቃዩ በኋላ የሕይወትን ብርሃን አይቶ ይረካል፤
በዕውቀቱም ብዙዎችን ያጸድቃል፤
በደላቸውንም ይሸከማል።
12ሕይወቱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፤
ከክፉ አድራጊዎችም ጋር ተቈጠረ፤
ይሁን እንጂ እርሱ የብዙዎችን ኃጢአት ተሸከመ፤
ለበደለኞችም ማለደ፤
ስለዚህ እኔ ከታላላቆቹ ጋር ድርሻ እንዲኖረውና
ከኀያላን ጋር ምርኮን እንዲካፈል አደርገዋለሁ።” #ማር. 15፥28፤ ሉቃ. 22፥37።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 53: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997