የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 5

5
ስለ ወይን ቦታ የተነገረ ግጥም
1ስለ ወይኑ ተክል
ለውዴ የፍቅር ዘፈን ልዝፈን
ውዴ እጅግ ለም በሆነ ኰረብታ ላይ
የወይን ተክል ነበረው።
2መሬቱን በመቈፈርና ድንጋዩንም ለቅሞ በማውጣት
ምርጥ የሆነውን የወይን ሐረግ ተከለበት፤
በመካከሉም መጠበቂያ የሚሆን ማማ ሠራለት፤
ጒድጓድ ቆፍሮም የወይን ፍሬ መጭመቂያ አበጀለት።
ከዚያን በኋላ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ ጠበቀ፤
ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ። #ማቴ. 21፥33፤ ማር. 12፥1።
3ስለዚህም ወዳጄ እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! በእኔና በወይን ተክል ቦታዬ መካከል ስላለው ነገር እስቲ ፍረዱ፤ 4ለመሆኑ እኔ ለእርሱ ያላደረግኹለት ነገር አለን? ከዚህስ ሌላ ላደርግለት የሚገባ ምን አለ? ታዲያ፥ መልካም ፍሬ ያፈራል ብዬ ስጠብቀው ስለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ?
5“እንግዲህ በወይን ቦታዬ ላይ የማደርገውን ልንገራችሁ፤ በዙሪያው ያለውን አጥር ነቃቅዬ ቅጽሩን አፈርሳለሁ፤ የምድር አራዊት እንዲበሉትና እንዲፈነጩበት አደርጋለሁ። 6ከዚያን በኋላ አይገረዝም፤ አይኰተኰትም፤ ስለዚህም አራሙቻ እንዲበቅልበት፥ በኲርንቺትና በእሾኽ እንዲሸፈን አደርጋለሁ፤ ዝናብም እንዳያዘንብበት ደመናን አዛለሁ።”
7ይህም የሠራዊት አምላክ የወይን ቦታ የተባለው
የእስራኤል ሕዝብ ነው፤
እርሱም የይሁዳ ሕዝብ ደስ የሚሰኝበት ተክል ነው።
መልካም ሥራ እንዲሠሩ ተስፋ ያደርግ ነበር፤
በዚህ ፈንታ ነፍሰ ገዳዮች ሆኑ፤
ቅን ፍርድ ይሰጣሉ ብሎ ተስፋ ያደርግ ነበር፤
እነርሱ ግን ፍርድን በማጓደላቸው የሕዝቡ ጩኸት በዛ።
የሰዎች ክፋት
8በአገሪቱ ላይ መኖር የሚገባችሁ እናንተ ብቻ መስሎአችሁ፥ ቀድሞ በነበራችሁ ይዞታ ላይ ለመቀላቀል ሰዎችን ሁሉ እያስወጣችሁ ቤትን ከቤት ማያያዝና እርሻንም በእርሻ ላይ ለመቀላቀል ለምትፈልጉ ወዮላችሁ! 9እነሆ የሠራዊት አምላክ እንዲህ ብሎ በመሐላ ሲያረጋግጥ ሰምቼአለሁ፦ “የተዋቡ ታላላቅ ቤቶች ሁሉ ፈርሰው ወና ይሆናሉ፤ የሚኖርባቸው ሰውም አይገኝም። 10በሩብ ጋሻ መሬት ላይ የተተከለው የወይን ፍሬ ስምንት ሊትር የወይን ጭማቂ ብቻ ይወጣዋል፤ አንድ መቶ ሰማኒያ ኪሎ እህል የተዘራበትም የእርሻ ምርት ዐሥራ ስምንት ኪሎ ብቻ ይገኝበታል።”
11ጠጥተው ለመስከር ማልደው ወደ መሸታ ቤት ለሚገሠግሡ፥ የወይን ጠጅ እስኪያቃጥላቸው ሌሊቱንም ሁሉ በዚያው መቈየት ለሚፈልጉ ወዮላቸው! 12በግብዣቸው ላይ መሰንቆና በገና፥ አታሞና እምቢልታ፥ የወይን ጠጅም ይገኛል፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ሥራና ውለታውን አላስተዋሉም፤ 13ስለዚህ ሕዝቤ ዕውቀት በማጣታቸው ተማርከው ይወሰዳሉ፤ የተከበሩ መሪዎቻቸው እስከ ሞት ድረስ ይራባሉ፤ ሕዝቡም በውሃ ጥም ይቃጠላል። 14መቃብር ሆድዋን አስፍታ፥ አፍዋን ከፍታ ትጠብቃቸዋለች፤ የኢየሩሳሌምን መሳፍንትና ተሰብስቦ የሚያወካ ሕዝብዋን ትውጣለች።
15ሰው ሁሉ የተዋረደ ጐስቋላ ይሆናል፤ ትዕቢተኛ የነበረውም ሁሉ ይዋረዳል። 16የሠራዊት አምላክ ግን በቅን ፍርዱ ከፍ ከፍ ይላል፤ ቅዱሱም አምላክ በእውነተኛነቱ ቅድስናውን ይገልጣል። 17የበግ ጠቦቶች፥ ቀድሞ ይሰማሩበት በነበረ ቦታ ይሰማራሉ፤ የሰቡ ፍሪዳዎችና የፍየል ግልገሎች በፈራረሱ ቦታዎች ሣር ይበላሉ።
18በማታለል ገመድ ኃጢአትን፥ በሠረገላ ገመድ ተንኰልን ለሚጐትቱ ወዮላቸው! 19“እኛ በዐይናችን እናያት ዘንድ እግዚአብሔር ሊያደርግ ያቀደውን በፍጥነት ያድርግ፤ እናውቃትም ዘንድ የእስራኤል ቅዱስ ያቀዳት ምክር ትፈጸም” ለሚሉ ሁሉ ወዮላቸው!
20ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑን ጨለማ ለሚያስመስሉ፥ ጣፋጩን መራራ፥ መራራውን ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!
21ራሳቸውን ብልኆችና ጥበበኞች አድርገው ለሚቈጥሩ ወዮላቸው!
22የወይን ጠጅ በመጠጣት ጀግኖች፥ የሚያሰክረውንም መጠጥ ለማደባለቅ ደፋሮች ለሆኑ ወዮላቸው! 23ጉቦ ተቀብለው በደል የሠራውን ሰው ነጻ በመልቀቅ፥ በደል የደረሰበትን ሰው ፍትሕ ለሚነፍጉ ወዮላቸው! 24የእስራኤል ቅዱስ የሠራዊት አምላክ ያዘዘውን ሕግና ያስተማረውን ሥርዓት ስለ አቃለሉ ገለባና ድርቆሽ በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ የእነርሱም ሥር መሠረት በስብሶ ይጠፋል፤ አበባቸውም ደርቆ እንደ ትቢያ ይበናል። 25እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ በጣም ተቈጥቶአል፤ በኀያልነቱም ይቀጣቸዋል፤ ተራራዎች ይናወጣሉ፤ የሞቱ ሰዎችም አስከሬን እንደ ጥራጊ በየመንገዱ ዳር ይወድቃል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ የእግዚአብሔር ቊጣ አይበርድም፤ እንደገናም ሊቀጣቸው ተዘጋጅቶአል።
26እግዚአብሔር አሕዛብን ከሩቅ የሚጠራበት ምልክት ያቆማል፤ ከምድር ዳርቻ ሁሉ በመጨረሻ ይጠራቸዋል፤ እነርሱም ፈጥነው እየተጣደፉ ይመጣሉ። 27በእነርሱ መካከል ደካማና የሚደናቀፍ አይገኝም፤ የሚያንቀላፋና የሚተኛም የለም፤ ትጥቃቸው አይፈታም፤ የጫማቸውም ማሰሪያ አይበጠስም። 28ፍላጻቸው የተሳለ፥ ቀስታቸው የተደገነ ነው፤ የፈረሶቻቸው ኮቴ እንደ ባልጩት ነው፤ የሠረገላዎቻቸውም መንኰራኲር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይገለባበጣል። 29ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤ እንደ ደቦል አንበሳ ያገሣሉ፤ ዕድናቸውን እያጒረመረሙ በመያዝ ይወስዳሉ፤ ማንም ሊያስጥላቸው አይችልም።
30በዚያን ቀን እንደ ባሕር ማዕበል እየተመሙ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ይመጡባቸዋል፤ እነሆ ወደ ምድር ቢመለከቱ በጨለማና በመከራ እንደ ተከበቡ ያያሉ፤ ከደመናውም የተነሣ ብርሃኑ ይጨልማል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ