ትንቢተ ኢሳይያስ 44
44
እግዚአብሔር ብቸኛ አምላክ መሆኑ
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የመረጥኳችሁ አገልጋዮቼ
የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ! አድምጡ።
2በማሕፀን የሠራኋችሁና
የምረዳችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤
አገልጋዮቼ ስለ ሆናችሁና እኔ ስለ መረጥኳችሁ አትፍሩ።
3“ለተጠማው ምድር ውሃን እሰጣለሁ፤
በደረቀውም ምድር ጅረቶች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤
መንፈሴን በልጆችህ ላይ አፈሳለሁ፤
በረከትንም ለልጅ ልጆችህ እሰጣለሁ።
4እነርሱ ውሃ በደንብ እንደ ጠጣ ሣር፥
በወራጅ ምንጮች አጠገብ እንዳለ የአኻያ ዛፍ
ሁልጊዜ የለመለሙ ይሆናሉ።
5“አንዱ ‘እኔ የእግዚአብሔር ነኝ’ ይላል፤
ሌላው በያዕቆብ ስም ይጠራል፤
ሌላው ደግሞ ‘የእግዚአብሔር ሰው ነኝ’ ብሎ በእጁ ላይ ይነቅሳል፤
እስራኤል በሚለውም ስም ይጠራል።”
6የሠራዊት አምላክ፥ የእስራኤል ንጉሥና አዳኝ እግዚአብሔር
እንዲህ ይላል፦
“የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤
ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም። #ኢሳ. 48፥12፤ ራዕ. 1፥17፤ 22፥13።
7እንደ እኔ ያለ ማነው?
እስቲ ካለ ይናገር፤
እስቲ ማስረጃውን በፊቴ ያቅርብ፤
ወደፊት የሚሆነውን አስቀድሞ የተናገረ ማነው?
እስቲ ወደፊት የሚሆነውን ይናገር።
8እናንተ አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤
ከጥንት ዘመናት ጀምሮ አስቀድሜ አልነገርኳችሁምን?
ወይስ አልገለጽኩላችሁምን?
ለዚህም እናንተ ምስክሮቼ ናቸሁ፤
ከእኔ ሌላ አምላክ አለን?
ከእኔ ሌላ መጠጊያ አለት የለም፤ ማንም የለም።”
በባዕድ አምልኮ ላይ የተደረገ የዘበት አነጋገር
9ጣዖቶችን የሚሠሩ ሁሉ ከንቱ ናቸው፤ ከፍተኛ ግምት የሚሰጡአቸው ጣዖቶቻቸውም ዋጋቢሶች ናቸው፤ በዚህም ኀፍረት ይደርስባቸዋል። 10አንድ ሰው ምንም የማይጠቅም ጣዖትን ወይም ምስልን ይሠራል? 11እነርሱንም የሚያመልኩ ሁሉ ያፍራሉ፤ ጣዖትን የሚሠሩ ሰዎች እንጂ ሌላ አይደለም፤ ሁሉም ይሰብሰቡና በፊቴ ይቁሙ፤ ሁሉም በፍርሃት ይዋጣሉ፤ ያፍራሉም።
12አንጥረኛ ጣዖትን ለመሥራት ብረትን ወስዶ በእሳት ያቀልጠዋል። ለብረቱም ቅርጽ ለመስጠት በብርቱ ክንዱ በመዶሻ ይቀጠቅጠዋል፤ ይህንንም በሚሠራበት ጊዜ ይራባል፥ ይጠማል፥ ይደክማልም።
13አናጢ በእንጨቱ ላይ መስመርን ያሰምራል፤ ንድፍም ይነድፋል፤ በመላጊያ ያለሰልሰዋል፤ በማስተካከያ መሣሪያም ትክክልነቱን ያረጋግጣል፤ ውበት ያለው የሰው ቅርጽ እንዲኖረው ያደርጋል። ከዚያም በጣዖት ቤት ያኖረዋል። 14ይህን ለማድረግ የሊባኖስ ዛፍ ወይም ዝግባ ዛፍ ወይም ዋርካ ከጫካው ይመርጣል፤ አለበለዚያም በአናጢው ተተክሎ የዝናብ ውሃ እየጠጣ የሚያድገውን የኮምበል ዛፍ ይተክላል። 15ሰው ከአንድ ዛፍ ግማሹን ለማገዶ፥ ግማሹንም ጣዖት ለመሥራት ይጠቀምበታል፤ ግማሹን እሳት አንድዶ ለመሞቅና እንጀራ ለመጋገር ይጠቀምበታል፤ በሌላው ጒማጅ ጣዖት ሠርቶ በፊቱ እየሰገደ ያመልከዋል። 16ግማሹን እሳት አንድዶ ምግቡን ያዘጋጅበታል፤ ሥጋም ጠብሶ እስከሚጠግብ ይመገባል፤ ከሞቀውም በኋላ “ግሩም እሳት ነው! እንዴት ይሞቃል!” ይላል። 17የቀረውንም ጒማጅ ጣዖት አድርጎ ይሠራና በፊቱ ተደፍቶ በመስገድ ያመልከዋል፤ “አንተ አምላኬ ነህ፤ አድነኝ!” እያለ ወደ እርሱ ይጸልያል።
18እንደዚህ ያሉት ሰዎች ዐይኖቻቸው ስለ ተሸፈኑ ማየት አይችሉም። 19“የዚህን እንጨት ግማሹን አነደድኩት፤ በፍሙም ዳቦ ጋገርኩበት፤ ሥጋም ጠብሼበት በላሁ፤ አሁን እንግዲህ ቀሪውን ቊራጭ እንጨት ለጣዖት ላውለውን? በአንድ ቊራጭ እንጨት ፊት ወድቄ ልስገድን?” ብሎ የሚያስብ ዕውቀት ወይም ማስተዋል ያለው አንድም ሰው የለም።
20ተቃጥሎ ዐመድ የሚሆነውን እንጨት እስከ ማምለክ ድረስ ሰው እንዴት ሞኝ ይሆናል? የሞኝነት አስተሳሰቡ አሳስቶታል፤ ራሱን ማዳን አይችልም፤ ወይም “ይህ በቀኝ እጄ ያለው ነገር ጣዖት እንጂ አምላክ አይደለም።” ብሎ መናገር አይችልም።
የእግዚአብሔር ፈጣሪነትና አዳኝነት
21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“እስራኤል ሆይ! ይህን አስታውስ፤
እኔ ፈጠርኩህ፤
አንተም አገልጋዬ መሆንህን አትርሳ፤
እኔም አልረሳህም።
22በደልህን እንደ ደመና ኃጢአትህን እንደ ማለዳ ጭጋግ አስወግጄአለሁ፤
ስለ አዳንኩህ ወደ እኔ ተመለስ።”
23ሰማያት ሆይ!
እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን በማዳን ክብሩን ገልጦአልና
በደስታ ዘምሩ፤ ምድርም ከታች እልል በዪ፤
ተራራዎች፥ ጫካዎችና በውስጣቸው የምትገኙ ዛፎች ሁሉ
የደስታ ድምፅ እያሰማችሁ ፈንድቁ።
24በእናትህ ማሕፀን የፈጠረህ አዳኝህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ሁሉን ነገር የፈጠርኩ፥ ሰማያትን ብቻዬን የዘረጋሁ፥
ምድርንም ብቻዬን ያነጠፍኩ፥
እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
25የሐሰተኞች ነቢያትን ምልክቶችና፥
የሟርተኞችን ጥንቈላ ከንቱ አደርጋቸዋለሁ።
የጥበበኞችን ዕውቀት እገለብጣለሁ፤
ዕውቀታቸውንም ወደ ሞኝነት እለውጠዋለሁ፤ #1ቆሮ. 1፥20።
26የአገልጋዮቼን መልእክት አጸናለሁ፤
የነቢያቴንም ትንቢት እንዲፈጸም አደርጋለሁ፤፥
እነርሱም ኢየሩሳሌም፦ ‘የብዙ ሕዝብ መኖሪያ ትሆናለች፤
የይሁዳ ከተሞችም እንደገና ይሠራሉ፤
ፍርስራሾቻቸውም ይታደሳሉ’ ይላሉ።
27ውቅያኖሱን ‘እኔ ወንዞችህን ስለማደርቅ
አንተ ድረቅ’ እለዋለሁ፤
28ቂሮስን ‘የመንጋዬ እረኛ ነህ፤
ዕቅዴን ሁሉ ትፈጽማለህ’ እለዋለሁ፤
ኢየሩሳሌምን ‘አንቺ እንደገና ትገነቢአለሽ’
ቤተ መቅደሱን፥ ‘መሠረትህ ይጣላል’
እላቸዋለሁ።” #2ዜ.መ. 36፥23፤ ዕዝ. 1፥2።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 44: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997