የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 43

43
እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመታደግ የሰጠው ተስፋ
1የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ!
የፈጠራችሁ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የታደግኋችሁ ስለ ሆነ አትፍሩ፤
እናንተ የእኔ ናችሁ፤
በስማችሁም ጠርቼአችኋለሁ።
2በውሃ ውስጥ በምታልፉበት ጊዜ
እኔ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ፤
በወንዞች መካከል በምታልፉበት ጊዜ አያሰጥሙአችሁም፤
በእሳትም ውስጥ በምታልፉበት ጊዜ አያቃጥላችሁም፤
ነበልባሉም ዐመድ አያደርጋችሁም።
3እኔ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር አምላካችሁና አዳኛችሁ ነኝ፤
እናንተን ለመታደግ ግብጽን፥ ኢትዮጵያውያንንና ሳባን እሰጣለሁ።
4እናንተ በእኔ ፊት የተወደዳችሁ ናችሁ፤
ስለምወዳችሁ ሕይወታችሁን ለማዳን
ሕዝቦችንና መንግሥታችን አሳልፌ እሰጣለሁ።
5እኔ ከእናንተ ጋር ስለ ሆንኩ አትፍሩ፤
ከምሥራቅም ከምዕራብም እናንተንና ልጆቻችሁን ሰብስቤ አመጣለሁ።
6“ወንዶች ልጆቼ ከሩቅ አገር እንዲመጡ
በሰሜን በኩል ያሉትን አገሮች ተዉአቸው፥
በደቡብ በኩል ያሉትን አገሮች ‘አትያዙአቸውም’ ብዬ አዛለሁ።
7እነርሱ በስሜ የተጠሩና ለክብሬ የፈጠርኳቸው
በእጄም የአበጀኋቸውና የሠራኋቸው ሕዝቤ ናቸው።”
እስራኤል የእግዚአብሔር ምስክር መሆኑ
8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ዐይን እያላቸው የማያዩ
ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ፥
ሕዝቤን በአንድነት ሰብስቡ!
9ሕዝቦች ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ፤
ከእነርሱ መካከል የአሁንና የቀድሞዎቹን ነገሮች አስቀድሞ የተናገረና የገለጠ ማነው?
እውነተኛነታቸውን ለማረጋገጥ ምስክሮቻቸውን ያምጡ።
እነርሱም ሰምተው እውነት ነው ይበሉ።
10“እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ተረድታችሁ
ታውቁኝና ታምኑብኝ ዘንድ የመረጥኳችሁ
አገልጋዮቼና ምስክሮቼ እናንተ ናችሁ።
በእርግጥ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤
ከእዚህ በፊት አልነበረም፤ ወደ ፊትም አይኖርም።
11“እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤
ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም
12እኔ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሜ ተናግሬአለሁ፤
እናንተን ያዳንኩ እኔ ነኝ፤
ከባዕዳን አማልክት አንድ እንኳ ይህን አላደረገም፤
ለዚህ ሁሉ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ።
13እኔ ከጥንት ጀምሮ አምላክ ነኝ፤
ከእጄ ማንም ማንንም አያድንም፤
እኔ ያደረግኹትን መለወጥ የሚችል የለም።”
ከባቢሎን ማምለጥ
14አዳኛችሁ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ስለ እናንተ በባቢሎን ላይ የሚዘምት ሠራዊት እልካለሁ፤
የከተማዋን ቅጽር በሮች እሰባብራለሁ፤
የባቢሎናውያንም ፉከራ ወደ ለቅሶ ይለወጣል።
15እኔ እግዚአብሔር የእናንተ ቅዱስ አምላክ ነኝ፤
እስራኤል ሆይ! እኔ ፈጠርኳችሁ፤
ንጉሣችሁም እኔ ነኝ።”
16እግዚአብሔር በባሕር መካከል መንገድን ሠራ፤
በውሃ መካከል መተላለፊያን አበጀ፥
17ሠረገሎችንና ፈረሶችን፥ የጦር ሠራዊትንና ጀግኖችን ወደ ጥፋታቸው መራቸው፤
እነርሱ ወደቁ፤ ዳግመኛም አይነሡም፤
እፍ ሲሉት እንደሚጠፋ ጧፍም ሆኑ።
18እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ያለፉትን ድርጊቶች አታስታውሱ፤
ከዚህ በፊት የሆነውንም ነገር አታሰላስሉ።
19ይልቅስ የማደርገውን አዲስ ነገር ተመልከቱ፤
እርሱም በመፈጸም ላይ ስለ ሆነ ልታዩት ትችላላችሁ፤
በበረሓ መንገድን አወጣለሁ፤
በምድረ በዳም ወንዞችን አፈልቃለሁ።
20ለተመረጡት ሕዝቤ ውሃን ለመስጠት
ወንዞች በበረሓ ጅረቶች በምድረ በዳ እንዲፈስሱ ባደረግሁ ጊዜ
የምድር አራዊት እንኳ ሳይቀሩ ያከብሩኛል፤
ቀበሮዎችና ሰጎኖችም ያመሰግኑኛል።
21እነርሱም ለራሴ የሠራኋቸው ሕዝቦች ስለ ሆኑ
እኔን ያመሰግናሉ።”
የእስራኤል ኃጢአት
22እግዚአብሔር እንዲህ ይላል!
“የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ፥
እናንተ ስሜን መጥራት ትታችኋል፤
ልታገለግሉኝም አልፈለጋችሁም።
23ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆኑ በጎቻችሁን አላቀረባችሁልኝም፤
በመሥዋዕታችሁም አላከበራችሁኝም፤
እኔም መባ እንድታቀርቡልኝ በመጠየቅ ሸክም አልሆንኩባችሁም፤
‘ዕጣን አቅርቡልኝም’ ብዬ አላሰለቸኋችሁም።።
24በገንዘባችሁ መልካም መዓዛ ያለው ዕጣን አልገዛችሁልኝም፤
ወይም በስብ መሥዋዕታችሁ አላረካችሁኝም፤
ነገር ግን በኃጢአታችሁ ብዛት ሸክም ሆናችሁብኝ።
በበደላችሁም ብዛት አሰለቻችሁኝ።
25ይህም ሁሉ ሆኖ
ኃጢአታችሁን ይቅር የምል አምላክ እኔ ነኝ፤
ይህንንም የማደርገው ስለ እናንተ ሳይሆን ስለ እኔነቴ ነው፤
ስለዚህ ኃጢአታችሁን አልቈጥርባችሁም።
26“አስታውሱኝ፤
ጉዳያችሁን አቅርባችሁ ትክክለኛነታችሁን አስመስክሩ።
27የመጀመሪያ አባታችሁ ኃጢአት ሠራ፤
አስተማሪዎቻችሁም በደል በመፈጸም እኔን አሳዘኑ።
28ስለዚህ የቤተ መቅደስን ሹማምንት ርኲሰት ገለጥኩ፤
የያዕቆብም ልጆች እስራኤላውያን እንዲዋረዱና
ፈጽመውም እንዲጠፉ አደረግሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ