ትንቢተ ኢሳይያስ 41
41
እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠው ተስፋ
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ በደሴቶች የምትኖሩ ሕዝቦች! ጸጥ ብላችሁ አድምጡ!
ሕዝቦች ኀይላቸውን ያድሱ፤
ወደ ፊትም ቀርበው ይናገሩ፤
በፍርድ ሸንጎ በአንድነት እንገናኝ።
2“ድል አድራጊውን አነሣሥቶ ከምሥራቅ ያመጣ፥
እንዲያገለግለው የጠራው ማነው?
ሕዝቦችን አሳልፎ ለእርሱ ይሰጣቸዋል።
ነገሥታትንም ያስገዛለታል፤
በሰይፉ እንደ ትቢያ በፍላጻዎቹም እንደ ገለባ ይበታትናቸዋል።
3ከዚህ በፊት እግሮቹ ሄደውበት በማያውቁት መንገድ
እነርሱን በፍጥነት ሲያሳድድ ምንም ጒዳት አይደርስበትም።
4ይህ እንዲሆን የፈቀደ ማን ነው?
የታሪክንስ ሂደት የሚቈጣጠር ማን ነው?
እኔ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ ነበርኩ፤
በመጨረሻም የምገኝ እኔው ነኝ።
5“በደሴቶች የሚኖሩ ሕዝቦች
እኔ ያደረግኹትን ሁሉ አይተዋል፤
ስለዚህም እጅግ ደንግጠው ተንቀጥቅጠዋል፤
በአንድነትም ተሰብስበው ወደ እኔ መጥተዋል።
6አንዱ ሌላውን ይረዳል፤
ወንድምም ወንድሙን ‘አይዞህ በርታ፤’ ይለዋል።
7የእጅ ጥበብ ዐዋቂው ወርቅ አንጥረኛን ያበረታታዋል፤
ጣዖት ጠርቦ በመዶሻ የሚያለሰልሰውም
በመስፍ ላይ የሚመታውን
‘አይዞህ በርታ! ብየዳው መልካም ነው!’ ይለዋል።
እንዳይንቀሳቀስም ጣዖቱን
በምስማር ይቸነክሩታል።” #41፥7 መስፍ፦ የጋለ ብረት ማስፊያ።
8“ነገር ግን አንተ አገልጋዬ እስራኤል ሆይ!
ሕዝቤ እንድትሆን የመረጥኩህ
የወዳጄ የአብርሃም ዘር ነህ። #2ዜ.መ. 20፥7፤ ያዕ. 2፥23።
9ከምድር ዳርቻ አመጣሁህ፥
ከአራቱም ማእዘን ጠራሁህ፤
‘አገልጋዬ ትሆናለህ’ ብዬ መረጥኩህ እንጂ አልጣልኩህም።
10እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ!
እኔ አምላክህ ነኝ፥ ተስፋ አትቊረጥ!
እኔ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፤
ድል ነሺ በሆነ ክንዴ እደግፍሃለሁ።
11በአንተ ላይ የተቈጡ ሁሉ ተሸንፈው ያፍራሉ፤
አንተንም ለመጒዳት የሚነሡ
ጠፍተው እንዳልነበሩ ይሆናሉ።
12ጠላቶችህን ትፈልጋቸዋለህ፤
ነገር ግን አታገኛቸውም፤
በአንተ ላይ ጦርነት አስነሥተው የነበሩትም
ፈጽሞ እንዳልነበሩ ይሆናሉ።
13‘አይዞህ አትፍራ፥ አትደንግጥ፥
ቀኝ እጅህን ይዤ እረዳሃለሁ’
እያልኩ የማበረታታህ፥
እኔ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።”
14እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
እንደ ትል ደካማ የሆንክ እስራኤል ሆይ!
እኔ ስለምረዳህ አትፍራ፤
የምታደግህ የእስራኤል ቅዱስ እኔ ነኝ።
15እነሆ፥ እኔ እንደ ስለታም፥ አዲስና፥ ጥርስ እንዳለው የመውቂያ መሣሪያ አደርግሃለሁ፤
ተራራዎችንም በማበራየት ታደቃቸዋለህ፤
ኰረብቶችንም ዳምጠህ እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ።
16ወደ ሰማይ ትበትናቸዋለህ፤
ነፋስም ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤
ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤
በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤
በእኔ በእስራኤል ቅዱስም ትመካለህ።
17“ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ አያገኙም፤
ጒሮሮአቸው ከጥማት የተነሣ ሲደርቅ፥
እኔ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እሰማለሁ፤
እኔም የእስራኤል አምላክ ከቶ አልተዋቸውም።
18በደረቁ ኰረብቶች ላይ ወንዞች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤
በሸለቆዎችም ውስጥ የውሃ ምንጮች ያልፋሉ፤
በረሓዎችንም የኲሬ ውሃ መከማቻ እንዲሆኑ አደርጋቸዋለሁ፤
ደረቁም ምድር የምንጭ ውሃ መፍሰሻ ይሆናል።
19የሊባኖስ ዛፎችን፥ የግራር እንጨቶችን፥
ባርሰነቱንና የወይራ ዛፎችን በበረሓ አበቅላለሁ፤
በምድረ በዳ ዝግባ፥ አስታና ጥድ፥ ወይራ የሞላበት ደን አበቅላለሁ።
20ይህን የማደርገው የእኔ የእግዚአብሔር እጅ ይህን
እንዳደረገና እኔም የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠርኩት
ሁሉም አይተው ያውቁ ዘንድ፥ አስተውለውም ይረዱ ዘንድ ነው።”
እግዚአብሔር ሐሰተኞች አማልክትን መቃወሙ
21የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፦ እንዲህ ይላል፦ “ጉዳያችሁን አቅርቡ፤
ማስረጃችሁንም አምጡ።
22ጣዖቶቻችሁንም አምጡና በሚፈጸምበት ጊዜ እንድናውቀው
ወደ ፊት የሚሆነውን ሁሉ እስቲ ይንገሩን፤
ወደፊት ውጤታቸው ምን እንደሚሆን አስተውለን እንረዳ ዘንድ
የቀድሞዎቹ ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ይንገሩን፤
ወይም ወደፊት ምን እንደሚከሠት ያስረዱን።
23እናንተም አማልክት መሆናችሁን እንድናውቅ
ወደ ፊት የሚሆነውን ሁሉ እስቲ ንገሩን፤
እስቲ መልካም ነገርን አድርጉ፤
ወይም አይተንላችሁ በመፍራት እንድንሸበር
ክፉ ነገርን ለማድረስ ሞክሩ።
24እናንተም ሆናችሁ ድርጊታችሁ በእርግጥ ከንቱ ነው፤
እናንተን ማምለክ የሚሹም አጸያፊዎች ናቸው።
25“እኔ እግዚአብሔር አንድ መሪ
ከሰሜን አስነሥቼአለሁ፤ መጥቶአልም።
እርሱም ስሜን የሚጠራና ከፀሐይ መውጫ በኩል የሚመጣ ነው።
ሸክላ ሠሪ የሸክላውን ዐፈር እንደሚረግጥ መሪዎችን ይረግጣል።
26እናውቀው ዘንድና ትክክል ነው እንል ዘንድ
ከመጀመሪያ ጀምሮ ይህን የተናገረ ማነው?
ስለዚህ ጉዳይ መግለጫ የሰጠ፥ ወይም ያወጀ፥ ከእናንተም
አንድ ቃል የተናገረ የለም።
27በመጀመሪያ ይህን ዜና ለጽዮን የገለጥኩላት እኔ ነኝ፤
ለኢየሩሳሌምም መልካም ዜና አብሣሪ የላክሁላት እኔ ነኝ።
28ዞር ብዬ በተመለከትኩ ጊዜ ማንም አልነበረም፤
ከአማልክትም መካከል ምክር የሚሰጥ አልነበረም፤
ጥያቄም ስጠይቅ ማንም መልስ የሚሰጥ አልነበረም።
29ስለዚህ እነዚህ አማልክት ሁሉ ከንቱ ናቸው፤
ምንም ነገር ሊያደርጉ አይችሉም፤
ምስሎቻቸውም እንደ ባዶ ነፋስ ናቸው።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 41: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997