የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 40:12-25

ትንቢተ ኢሳይያስ 40:12-25 አማ05

ውቅያኖስን በእፍኙ፥ ሰማይንም በስንዝሩ፥ የምድርን ዐፈር በቊና መለካት የሚችል ማን ነው? ተራራዎችንና ኰረብቶችንስ በሚዛን የሚመዝን ማን ነው? እግዚአብሔርን “እንዲህ አድርግ” ብሎ የሚያዘው ማን ነው? እርሱን ማስተማርና መምከር የሚችልስ ማን ነው? ያብራራለት ዘንድ እግዚአብሔር ማንን አማከረ? ትክክለኛውን ፍርድ ያስተማረው ማነው? ዕውቀትን ያስተማረው፥ ወይም ትክክለኛውን መንገድ እንዲያስተውል ያደረገው ማነው? በእግዚአብሔር ፊት ሕዝቦች እንደ አንድ የውሃ ጠብታ ናቸው፤ በሚዛንም ላይ እንዳለ ዐቧራ ናቸው፤ ደሴቶችም በእርሱ ዘንድ እንደ ትቢያ የቀለሉ ናቸው። በሊባኖስ የሚገኙ እንስሳት ሁሉ ለአምላካችን የሚቃጠል መሥዋዕት ለመሆን፥ ከሚፈለገው ቊጥር ያነሱ ናቸው። ዛፎቹም ሁሉ የመሥዋዕቱን እሳት ለማቀጣጠል አይበቁም። በእግዚአብሔር ዘንድ ሕዝቦች ሁሉ እንዳሉ የሚቈጠሩ አይደሉም። እነርሱ በእርሱ ዘንድ እንደ ኢምንት የሚቈጠሩና ዋጋ የሌላቸው ናቸው። እግዚአብሔርን ከማን ጋር ታነጻጽሩታላችሁ? ከማንስ ጋር ታመሳስሉታላችሁ? እርሱ እኮ እንጨት ጠራቢ እንደሚቀርጸው፥ አንጥረኛም በወርቅ እንደሚለብጠው በብር ሠርቶ እንደሚያቆመው ጣዖት ዐይነት አይደለም። ሀብት የሌለው ድኻ ለመባው በማይነቅዝ ልዩ እንጨት ይመርጥና በግንባሩ እንዳይደፋ ብልኀተኛ አስተካክሎ እንዲሠራው ያደርጋል። ከቶ ይህን አታውቁምን? አልሰማችሁምን? ከመጀመሪያው ጀምሮ አልተነገራችሁምን? ምድር ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ አላስተዋላችሁምን? እግዚአብሔር ከምድር ክበብ በላይ ዙፋኑን ዘርግቶ መቀመጡን ሰማይን እንደ መጋረጃ መወጠሩንና፥ እንደ መኖሪያ ድንኳን መዘርጋቱን የምድርም ሕዝቦች እንደ ፌንጣ አነስተኞች መሆናቸውን። እርሱ ልዑላንን ያዋርዳል፤ የዚህ ዓለም ገዢዎችንም እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል። እነርሱ ገና እንደ በቀለና ሥር እንዳልሰደደ አዲስ ተክል ናቸው፤ እግዚአብሔር ነፋሱን ሲልክ ወዲያውኑ ይደርቃሉ፤ እንደ ገለባም በነው ይጠፋሉ። “ታዲያ፥ እኔን ከማን ጋር ታነጻጽሩኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታመሳስሉኛላችሁ?” ይላል ቅዱስ እግዚአብሔር።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}