የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 37

37
ንጉሥ ሕዝቅያስ የኢሳይያስን ምክር መጠየቁ
(2ነገ. 19፥1-7)
1ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደ። 2የቤተ መንግሥቱን አዛዥ ኤልያቄምን፥ የቤተ መንግሥቱን ዋና ጸሐፊ ሼብናንና ከካህናት መካከል ታዋቂዎች የሆኑትን ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ላከ፤ እነርሱም ማቅ ለብሰው ነበር። 3እነርሱም ከሕዝቅያስ ተቀብለው ለኢሳይያስ የነገሩት መልእክት ይህ ነበር፦ “ዛሬ የታላቅ መከራ ቀን ነው፤ የሚያሳፍር ቅጣትና ውርደት እየደረሰብን ነው፤ የምትወልድበት ጊዜ ደርሶ ለማማጥ አቅም እንዳነሣት ሴት ሆነናል፤ 4የአሦር ንጉሥ ሕያው እግዚአብሔርን እንዲሰድብለት ከፍተኛ ባለሥልጣኑን ልኮአል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ስድብ ሰምቶ ተሳዳቢውን ይቀጣ ይሆናል፤ ስለዚህ ከሕዝባችን መካከል በሕይወት ስለሚተርፉት እባክህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ።” 5ኢሳይያስም ንጉሥ ሕዝቅያስ የላከውን መልእክት ሰምቶ፥ 6ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ላከ፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች እኔን የሰደቡበትን የስድብ ቃል በመስማትህ አትፍራ።’ 7በሀገሩ ስላለ ጉዳይ በሹክሹክታ ወሬ እንዲሸበርና ወደ ሀገሩ ተመልሶ በሰይፍ እንዲገደል አደርገዋለሁ።”
አሦራውያን ሌላ የዛቻ መልእክት መላካቸው
(2ነገ. 19፥8-19)
8የአሦራውያን ባለ ሥልጣን ንጉሡ ላኪሸን ለቆ በአቅራቢያ ወዳለችው ወደ ሊብና ከተማ በመሄድ እዚያ በመዋጋት ላይ መሆኑን ሰማ፤ ስለዚህ ወደዚያ ሄደ። 9በኢትዮጵያ ንጉሥ በቲርሃቃ የሚመራ የግብጽ ሠራዊት እነርሱን ለመውጋት በመገሥገሥ ላይ መሆኑን አሦራውያን ሰሙ፤ የአሦር ንጉሥ ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ በመልእክተኛ እጅ ላከ፦ 10“የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሆይ! የምትታመንበት አምላክ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም!’ ብሎ ተስፋ በመስጠት አያታልህ። 11የአሦር ነገሥታት አንድን አገር ለማጥፋት በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ እንዴት እንደሚያወድሙአት ሰምተሃል፤ ታዲያ፥ አንተስ ከዚህ የምታመልጥ ይመስልሃልን? 12የቀድሞ አባቶቼ የጎዛንን፥ የካራንና የሬጼፍን ከተሞች አጥፍተዋል፤ በተላሳር ይኖሩ የነበሩትን የዔደንን ሕዝብ ገድለዋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ከአማልክታቸው አንዳቸው እንኳ ሊያድኑአቸው ችለዋልን? 13የሐማት፥ የአርፋድ፥ የሰፋርዋይም የሄናዕና የዒዋ ከተሞች ነገሥታት አሁን ወዴት አሉ?”
የሕዝቅያስ ጸሎት
14ንጉሥ ሕዝቅያስ ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ ቤተ መቅደስም ወስዶ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት በማቅረብ፥ 15እንዲህ ሲል ጸለየ 16“የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክ ሆይ! በኪሩቤል ላይ ዙፋን የዘረጋ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤ የዓለምም መንግሥታት ሁሉ አምላክ አንተ ነህ፤ ሰማይና ምድርን የፈጠርክ አንተ ነህ። #ዘፀ. 25፥22። 17አምላክ ሆይ! ሰናክሬም! እንዴት አድርጎ አንተን ሕያው አምላክን እንደ ዘለፈ ተመልከት። 18አምላክ ሆይ! የአሦር ነገሥታት ብዙ መንግሥታትን ማጥፋታቸውንና ምድራቸውንም መደምሰሳቸውን ሰምተናል። 19እንጨቱን በመጥረብ፥ ድንጋዩን በማለዘብ በሰው እጅ የተሠሩ ከንቱ የሆኑ አማልክታቸውን በእሳት አቃጥለው አጥፍተዋል። 20እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ያውቁ ዘንድ አሁን ከአሦራውያን እጅ በመታደግ አድነን።”
ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ያስተላለፈው መልእክት
(2ነገ. 19፥2-37)
21ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ዛቻ ያቀረብከውን ጸሎት ሰምቼአለሁ፤’ 22ስለ እርሱም እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፥ ‘ሰናክሬም ሆይ! የኢየሩሳሌም ሕዝብ አንተን በመናቅ ያፌዙብሃል፤ በምትሸሽበትም ጊዜ ከበስተኋላህ ሆነው ራሳቸውን ይነቀንቁብሃል። 23ዐይንህን በትዕቢት አቅንተህ፥ ድምፅህን ከፍ አድርገህ በመጮኽ የተዳፈርከውና የተሳደብከው ማንን ይመስልሃል? የእስራኤልን ቅዱስ አይደለምን?’ 24አገልጋዮችህን ልከህ በጌታ ላይ የስድብ ቃል በመናገር፦ ‘በሠረገሎቼ ብርታት ከፍተኛ የሆኑ የሊባኖስ ተራራዎችን ይዤአለሁ፤ ረጃጅም የሆኑትን የሊባኖስ ዛፎችና የተዋቡ የዝግባ ዛፎችን ቈርጬአለሁ፤ በከፍተኛ ስፍራዎች ላይ ጥቅጥቅ ወዳሉት ደኖች አልፌአለሁ፤ 25በባዕዳን አገሮች ጒድጓዶችን ቆፍሬ ውሃ ጠጥቻለሁ፤ የብዙ ሠራዊቴ እግር የግብጽን ወንዞች አድርቋል’ ብለህ ተመክተሃል።
26“ከብዙ ጊዜ በፊት ይህን ሁሉ የወሰንኩት እኔ ራሴ መሆኔን አልሰማህምን? ዕቅዱን አውጥቼ አሁን ለፍጻሜ ያደረስኩት እኔ ነኝ፤ የተመሸጉ ከተሞችን የፍርስራሽ ክምር እንድታደርጋቸው ኀይልን የሰጠሁህ እኔ ነኝ። 27የሕዝቦቻቸው ኀይል ተዳክሞአል፤ እነርሱም ተስፋ ቈርጠው ዐፍረዋል፤ እንደ ሜዳ አበባ፥ እንደ ለጋ ሣር፥ በጣራ ላይ እንደሚበቅልና ፈጥኖ እንደሚጠወልግ ጓሳ ናቸው።
28“እኔ ስለ አንተ ሁሉን ነገር ዐውቃለሁ፤ ምን እንደምታደርግና ወዴት እንደምትሄድ እመለከታለሁ፤ በእኔ ላይ በቊጣ መነሣሣትህንም ተረድቼአለሁ። 29በእኔ ላይ ስለ መቈጣትህና ስለ ልብህ ትዕቢት ሁሉ ሰምቼአለሁ፤ ስለዚህ አሁን በአፍንጫህ ስናጋ፥ በአፍህም ልጓም አግብቼ በመጣህበት መንገድ እመልስሃለሁ።”
30ከዚህ በኋላ ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሁሉ እንደሚፈጸም ምልክቱ ይህ ነው፦ በአሁኑና በሚቀጥለው ዓመት ሳይዘሩት የበቀለውንና የገቦውን እህል ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ግን የራሳችሁን እህል ዘርታችሁ ታመርታላችሁ፤ ወይንም ተክላችሁ ፍሬውን ትበላላችሁ። 31በይሁዳ ከጥፋት የተረፉት ሁሉ ወደ መሬት ሥር ሰዶ እንደሚያድግና እንደሚያፈራ ተክል ይሆናሉ። 32ይህ ሁሉ እንዲፈጸም የሠራዊት አምላክ ቅናት ስለ ወሰነ ከኢየሩሳሌምና ከጽዮን ኰረብታ ከጥፋት የሚተርፉ ይኖራሉ።
33“ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ አሦራውያን ንጉሥ የተናገረውም ቃል ይህ ነው፤ ‘ሰናክሬም ወደዚህች ከተማ ፈጽሞ አይገባባትም፤ አንድ ፍላጻ እንኳ አይወረውርባትም፤ ጋሻ ያነገበ ወታደርም ወደ እርስዋ አይቀርብም፤ በዐፈር ቊልልም አትከበብም። 34ስለዚህም እርሱ ወደዚህች ከተማ ሳይገባ በመጣበት መንገድ ተመልሶ ይሄዳል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 35ስለ ራሴ ክብርና ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ይህችን ከተማ እኔ ራሴ በመከላከል አድናታለሁ።’ ”
36በዚያው ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አሦራውያን ሰፈር አልፎ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ወታደሮችን ገደለ፤ በማግስቱ በማለዳ ሰዎች በሚነቁበት ጊዜ ሁሉም ሞተው ተገኙ። 37ከዚህ በኋላ የአሦራውያን ንጉሥ ሰናክሬም ወደኋላው በማፈግፈግ ወደ ነነዌ ተመልሶ በዚያ ኖረ። 38ከዕለታት በአንዱ ቀን ኒሰሮክ በሚል ስም በሚጠራው ጣዖት ቤተ መቅደስ ውስጥ በስግደት ላይ እንዳለ ከልጆቹ ሁለቱ በተለይ አድራሜሌክና ሣሬጼር ተብለው የሚጠሩት በሰይፍ ገደሉት፤ እነርሱም ወደ አራራት አምልጠው ሄዱ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ከልጆቹ አንዱ አስራዶን የተባለው ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ