የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 38

38
ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ ስለ መዳኑ
(2ነገ. 20፥1-112ዜ.መ. 32፥24-26)
1በዚያን ዘመን ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ለመሞት ተቃርቦ ነበር፤ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ሊጐበኘው ወደ እርሱ ሄዶ “እግዚአብሔር ‘ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህም ስለማይቀር ቤትህን አዘጋጅ’ ብሎሃል” ሲል ነገረው።
2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፦ 3“አምላክ ሆይ! በታማኝነትና በሙሉ ልብ እንዳገለገልኩህ፥ አንተ የምትደሰትበትንም ነገር እንዳደረግሁ አስታውስ፤” ምርር ብሎም አለቀሰ።
4ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ኢሳይያስን እንዲህ አለው፦ 5“ወደ ሕዝቅያስ ሄደህ እንዲህ በለው፤ ‘እነሆ፥ የቀድሞ አባትህ የዳዊት አምላክ እኔ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰምቼአለሁ፤ እንባህንም አይቼአለሁ፤ ስለዚህም በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨምሬልሃለሁ፤ 6አንተንና ይህችን የኢየሩሳሌምን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ከተማይቱንም በመከላከል እጠብቃለሁ።’ ”
7ኢሳይያስም እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም ስለ መሆኑ የሚሰጥህ ምልክት ይህ ነው፤ 8ንጉሥ አካዝ ባሠራው የመወጣጫ ደረጃ ላይ የሚያርፈውን ጥላ እግዚአብሔር እንደገና ዐሥር ደረጃዎችን አልፎ ወደ ኋላ እንዲመለስ ያደርገዋል።” ጥላውም ዐሥር ደረጃዎችን አልፎ ወደ ኋላ ተመለሰ።
9ሕዝቅያስም ከሕመሙ እንደ ተፈወሰ የሚከተለውን የምስጋና መዝሙር ጻፈ፦
10እኔ ገና በመካከለኛ ዕድሜዬ ሳለሁ የመኖር ዕድል ተነፍጎኝ
ወደ ሙታን ዓለም የምወርድ መስሎኝ ነበር።
11ሕያዋን በሚኖሩበት በዚህ ዓለም እግዚአብሔርን
ወይም ከሕያው ፍጡር ሁሉ መካከል ሰውን
ዳግመኛ አላይም ብዬ ነበር።
12ሕይወቴ በድንገት እንደ እረኛ ድንኳን የተነቀለና የተጠቀለለ፥
ተሠርቶም ሳያልቅ ከሸማኔው መጠቅለያ እንደ ተቈረጠ ልብስ ሆነ ብዬ አስቤ ነበር፤
እግዚአብሔር ሕይወቴን በአጭር የቀጫት መስሎኝ ነበር።
13እስከ ንጋት ድረስ ስጮኽ ዐድራለሁ፤
እንደ አንበሳም አጥንቶቼን ሁሉ ሰባበርክ፤
ሌሊትና ቀንም ለሥቃይ አሳልፈህ ሰጠኸኝ።
14እንደ ሽመላ እጮኽ ነበር፤
እንደ ርግብ የሐዘን ድምፅ አሰማ ነበር፤
ወደ ሰማይም አሻቅቤ ከመመልከቴ የተነሣ፥
ዐይኖቼ በጣም ደክመው ነበር።
ጌታ ሆይ! እባክህን ከዚህ ሁሉ መከራ አድነኝ!
15ይህን ሁሉ ያደረገው እግዚአብሔር ራሱ ስለ ሆነ፥
ምን ማለት እችላለሁ?
ከምሬቴ የተነሣ እንቅልፌ ሁሉ ጠፍቶ ነበር።
16ነፍሴ ካንተ ሕይወትን ታገኛለች፤
ለመንፈሴ ዕረፍትን ስጣት፤
ጤንነቴን እንደ ነበረ አድርግልኝ፥
ሕይወትንም ስጠኝ።
17ችግር የደረሰብኝ በእርግጥ ለደኅንነቴ ነው፤
ከአደጋም ሁሉ ሕይወቴን ታድናለህ፤
ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር ትላለህ።
18ከሙታን ዓለም ሊያመሰግንህ የሚችል አንድ እንኳ የለም፤
ሙታንም ሊያመሰግኑህ አይችሉም፤
ወደ መቃብር የወረዱትም ታማኝነትህን ተስፋ አያደርጉም።
19እኔ አሁን እንደማመሰግንህ
ሊያመሰግኑህ የሚችሉት ሕያዋን ብቻ ናቸው፤
አባቶች ለልጆቻቸው የአንተን ታማኝነት ይናገራሉ።
20እግዚአብሔር ያድነኛል፤
ስለዚህ እኛ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ
አውታር ባለው የሙዚቃ መሣሪያ
የምሥጋና መዝሙር
በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዘምራለን።
21ከዚህ በኋላ ኢሳይያስ የበለስ ቅጠሎችን ጥፍጥፍ በእባጩ ላይ ቢያደርጉ ይፈወሳል ብሎአቸው ነበር።
22ንጉሥ ሕዝቅያስም “ድኜ ወደ ቤተ መቅደስ ለመሄድ እንደምችል የማውቀው በምን ምልክት ነው?” ሲል ኢሳይያስን ጠየቀ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ