የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 35

35
የቅድስና አገር
1በረሓውና ደረቁ ምድር ደስ ይለዋል፤
በምድረ በዳም አበቦች ያብባሉ።
2ምድረ በዳዎች በፈኩ አበቦች ይሞላሉ፤
የደስታ መዝሙርም ይዘምራሉ፤
እንደ ሊባኖስ ተራራ ግርማ ያላቸው ይሆናሉ፤
እንደ ቀርሜሎስም ተራራ ወይም እንደ ሻሮን ሸለቆ ክብርን የተጐናጸፉ ይሆናሉ።
ሁሉም የእግዚአብሔርን ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።
3የደከሙትን ክንዶች አጠንክሩ፥
የተብረከረኩ ጒልበቶችንም አጽኑ። #ዕብ. 12፥12።
4ፈሪ ልብ ላላቸው “እነሆ አምላካችሁ ጠላቶቻችሁን ለመበቀልና
የበደላቸውንም ዋጋ ለመክፈል መጥቶ ስለሚያድናችሁ
በርቱ! አትፍሩ!” በሉአቸው።
5በዚያን ጊዜ ዕውሮች ያያሉ፤
ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤
6አንካሶች እንደ ሚዳቋ ይዘላሉ፤
መናገር የማይችሉ ድዳዎች ይዘምራሉ፤
በበረሓ ውስጥ የጅረት ውሃ ይፈስሳል። #ማቴ. 11፥5፤ ሉቃ. 7፥22።
7የሚያቃጥለው አሸዋ ኩሬ ይሆናል፤
ደረቁም ምድር በምንጭ ውሃ ይረሰርሳል፤
የቀበሮዎች መፈንጫ የነበረው ስፍራ
ለምለም ሣርና ቄጠማ የሚበቅልበት ይሆናል።
8በዚያ “ቅዱስ ጐዳና” የሚባል መንገድ ይኖራል፤
እርሱም ለእግዚአብሔር ሰዎች ይሆናል፤
ንጹሕ ያልሆነ ሰው በዚያ መንገድ አይሄድም፤
ሞኞችም ሊሄዱበት አይችሉም።
9አንበሶችም ሆነ ነጣቂ አውሬዎች በዚያ አይገኙም፤
በዚያ መንገድ የሚመላለሱ
እግዚአብሔር የታደጋቸው ወገኖች ብቻ ይሆናሉ።
10እግዚአብሔር የታደጋቸው ሰዎች ተመልሰው ይመጣሉ፤
እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይገባሉ፤
ዘወትር የደስታን ዘውድ ይቀዳጃሉ፤
ተድላና ደስታንም ያገኛሉ፤
ማዘንና መቃተት ከእነርሱ ይርቃል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ