ትንቢተ ኢሳይያስ 33
33
ርዳታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት
1አንተ ማንም ጥፋት ሳያደርስብህ ጥፋተኛ የሆንክ! ማንም ሳይከዳህ ከዳተኛ የሆንክ ወዮልህ! ጥፋትን ማድረስህን ስታቆም ትጠፋለህ፤ ከዳተኛነትህንም ስታቆም ክዳት ይደርስብሃል።
2አምላክ ሆይ! አንተን ተስፋ እናደርጋለንና ማረን! ማረን! በየቀኑ ጥበቃህ አይለየን፤ በመከራ ጊዜም ታደገን። 3የአንተ ድምፅ እንደ መብረቅ በሚበርቅበት ጊዜ ሕዝቦች ይሸሻሉ፤ ከግርማህም የተነሣ መንግሥታት ይበተናሉ። 4አንበጣ እንደሚሰበሰብ ምርኮ ይሰበሰባል፤ ኩብኩባዎች እንደሚዘሉ ሰዎች በምርኮው ላይ ይረባረባሉ።
5እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ነው! በሰማያትም ይኖራል፤ ለጽዮንም ጽድቅንና ፍትሕን ያጐናጽፋል። 6የሕዝቡ መሠረት እርሱ ነው፤ ለሕዝቡ ደኅንነትን፥ ጥበብንና ዕውቀትን ይሰጣል፤ እግዚአብሔርን መፍራትም ትልቁ ሀብታቸው ይሆናል።
7ጀግኖች በመንገድ ላይ ለእርዳታ እንዴት እንደሚጮኹ፥ ለሰላም የተላኩትም መልእክተኞች እንዴት ምርር ብለው እንደሚያለቅሱ ተመልከቱ። 8አውራ ጐዳናዎች ባዶ ሆኑ፤ በመንገዶቹ ላይ ተጓዦች የሉም፤ ቃል ኪዳን ፈረሰ፤ የውል ስምምነቶች ተጥሰዋል፤ ከዚህም የተነሣ ምክር የሚሰጠው ሰው አልተገኘም። 9ምድሪቱም ደርቃለች፤ ባድማ ሆናለች፤ የሊባኖስ ደኖች ደርቀዋል፤ ለሙ የሳሮን ሸለቆ ወደ በረሓነት ተለውጦአል፤ በባሳንና በቀርሜሎስ ተራራዎች የሚገኙ ዛፎች ቅጠላቸው ረግፎአል።
እግዚአብሔር ለሚጠሉት ሁሉ የሰጠው ማስጠንቀቂያ
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አሁን እኔ እነሣለሁ፤ እከበራለሁ፤ ከፍ ከፍም እላለሁ። 11ገለባን ፀንሳ እብቅ እንደምትወልድ እስትንፋሳችሁ እንደ እሳት ሆኖ ያጋያችኋል። 12እናንተ ለኖራ እንደሚቃጠሉና ለእሳት እንደሚቈረጥ እሾኽ ትሆናላችሁ። 13እናንተ በሩቅ ያላችሁ የሠራሁትን ስሙ፤ እናንተም በቅርብ ያላችሁ ኀያልነቴን አረጋግጡ።”
14በጽዮን ያሉ ኃጢአተኞች ይፈራሉ፤ ከሐዲዎችም ይርበደበዳሉ፤ ከእኛ መካከል ከሚባላ እሳትና ከዘለዓለማዊ ነበልባል ጋር ለመኖር የሚችል ማነው ይላሉ። 15በእውነትና በትክክል የሚናገሩ፥ በግፍ የሚገኝን ትርፍ የሚጸየፉ፥ ጉቦን ከመቀበል ይልቅ የሚያስወግዱ፥ ስለ ነፍስ ግድያ መስማት የማይፈልጉና፥ ክፉ ነገርን ከማየት ዐይኖቻቸውን የሚጨፍኑ፥ 16በከፍተኛ ቦታ ላይ ይኖራሉ። ከለላቸውም እንደ ቋጥኝ ምሽግ ይሆናል ምግባቸውንም በጊዜው ያገኛሉ፤ የሚጠጡትንም ውሃ አያጡም።
ወደፊት የሚመጣው ክብር የሞላበት ዘመን
17በአራቱ ማእዘን ወሰንዋ በሰፊ ምድር ላይ ውበት ባለው ግርማ የሚያስተዳድረውን ንጉሥ ታያላችሁ፤ 18በሐሳባችሁ ቀድሞ ይደርስባችሁ የነበረውን ሽብር በማስታወስ “ኀላፊው የት አለ? ግብር ሰብሳቢው የት አለ? የዘብ ኀላፊውስ የት አለ?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ። 19እናንተ ልታስተውሉትና ልትረዱት በማትችሉት ቋንቋ የሚንተባተቡባችሁን እብሪተኞች ባዕዳን ሕዝቦችን ከእንግዲህ ወዲህ አታዩአቸውም። 20የታወቁ የሃይማኖት በዓላትን የምናከብርባትን የጽዮንን ከተማ ተመልከቱ፤ በሰላም ትኖሩባት ዘንድ ምቹ የሆነችውን ኢየሩሳሌምን እዩ! ካስማዎቹ ከቶ እንደማይነቀሉ፥ ገመዶቹም እንደማይበጠሱና ከስፍራው እንደማይንቀሳቀስ ድንኳን ትሆናለች። 21እዚያም ማንም ጀልባዎችን በማይቀዝፍባቸውና ትላልቅ መርከቦች በማይንሳፈፉባቸው በወንዞችና በሰፋፊ ጅረቶች እግዚአብሔር በታላቅ ግርማው ከእኛ ጋር ይሆናል። 22እግዚአብሔር ዳኛችን፥ ሕግ ሰጪአችንና ንጉሣችን ነው፤ የሚያድነንም እርሱ ነው፤ 23ሕዝባችሁ ግን የምሰሶው ገመድ እንደ ላላ ምሰሶውም እንዳልጸና፥ ሸራውም እንዳልተዘረጋ መርከብ ነው፤ ከዚያ በኋላ የተትረፈረፈ ምርኮ ይከፋፈላል፤ አንካሶች እንኳ ገብተው ይበዘብዛሉ። 24ከጽዮን ነዋሪዎች መካከል “አመመኝ!” የሚል አይኖርም፤ በዚያም ለሚኖሩ ሁሉ የኃጢአት ይቅርታ ይደረግላቸዋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 33: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997