የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 31

31
በግብጽ ላይ የመተማመን ከንቱነት
1ብዙ ፈረሶች፥ ሠረገሎችና ወታደሮች ባሉት ብርቱ በሆነው በግብጽ ሠራዊት ተማምነው ርዳታ ለማግኘት ወደ ግብጽ ለሚወርዱ ወዮላቸው! ነገር ግን የእስራኤልን ቅዱስ ርዳታ አይለምኑም፤ መመሪያውንም አይቀበሉም። 2ሆኖም እግዚአብሔር ጥበበኛ ነው፤ መቅሠፍትንም ያመጣል፤ ቃሉን አያጥፍም፤ በክፉ ሰዎች ቤት ላይና ክፉዎችን በሚረዱ ሰዎች ላይ ይነሣል። 3ግብጻውያን ሰዎች ናቸው እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ ለባሾች እንጂ የተለዩ መናፍስት አይደሉም፤ እግዚአብሔር በቊጣው በሚነሣበት ጊዜ ይህ የሌሎች ረዳት የሆነው መንግሥት ይደናቀፋል፤ እርሱ ይረዳው የነበረውም መንግሥት ተንኰታኲቶ ይወድቃል፤ ሁለቱም በአንድነት ተያይዘው ይጠፋሉ።
እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን የሚታደግ መሆኑ
4እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “አንበሳ በገደለው እንስሳ ላይ በሚያገሣበት ጊዜ እረኞች ተጠራርተው የቱንም ያኽል ቢጮኹ የእነርሱ ጩኸት ምንም እንደማያስፈራው እኔም የሠራዊት አምላክ የጽዮንን ተራራና ኰረብቶቿን ለመከላከል የሚያግደኝ የለም። 5ወፍ በጎጆዋ ላይ ክንፍዋን ዘርግታ በማንጃበብ ጫጩቶችዋን እንደምትጠብቅ፥ እኔ የሠራዊት አምላክ ኢየሩሳሌምን እጋርዳታለሁ፤ እጠብቃታለሁ፤ አድናታለሁ፤ ከችግር አወጣታለሁ።
6“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ፈጽማችሁ ወደ ከዳችሁኝ ወደ እኔ ተመለሱ! 7በኃጢአተኛ እጃችሁ ከብርና ከወርቅ የሠራችኋቸውን ጣዖቶቻችሁን ሁሉ አሽቀንጥራችሁ የምትጥሉበት ጊዜ ይመጣል። 8ከዚያ በኋላ አሦራውያን የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃሉ። 9ሽብር በተነሣ ጊዜ ምሽጋቸው ይፈርሳል፤ የጦር መኰንኖቻቸውም አርማቸውን ትተው በመርበድበድ ይሸሻሉ”። እሳቱ በጽዮን፥ እቶኑ በኢየሩሳሌም የሆነው እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ