የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 21

21
የባቢሎንን አወዳደቅ የሚያመለክት ራእይ
1በባሕር አጠገብ ስለሚገኝ ምድረ በዳ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
ከደቡብ በኩል የሚመጣው ዐውሎ ነፋስ ሁሉን ነገር ጠራርጎ እንደሚወስድ አስፈሪ ከሆነች ከአንዲት አገር ከባድ ጥፋት ይመጣል። 2አስፈሪ የሆነ ራእይ ተገልጦልኛል፤ ይኸውም አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ ከዳተኛው ይከዳል፤ ዘራፊውም ይዘርፋል።
የዔላም ሠራዊት ሆይ! አደጋ ለመጣል ውጡ! የሜዶን ሠራዊት ሆይ! ከተሞችን ክበቡ! እግዚአብሔር በባቢሎን ምክንያት የደረሰውን ሥቃይ ሁሉ ያስወግዳል።
3በዚህም ምክንያት ሰውነቴ ታመመ፤ ምጥ እንደ ያዛት ሴትም አስጨነቀኝ፤ በምሰማው ነገር ታወክሁ፤ በማየውም ነገር ግራ ተጋባሁ። 4ራሴን ያዞረኛል፤ ከፍርሃት የተነሣም እንቀጠቀጣለሁ፤ ቀኑ ቶሎ እንዲመሽልኝ ተመኘሁ፤ ተስፋ ያደረግኹት ጭላንጭል አስደንጋጭ ሆነብኝ፦
5ባየሁትም ራእይ ግብዣ ተዘጋጅቶ ለእንግዶች መቀመጫ ስጋጃዎች ተነጥፈዋል፤ እነርሱም ገና በመብላትና በመጠጣት ላይ ሳሉ፥ “እናንተ የጦር መኰንኖች! ጋሻችሁን ወልውላችሁ አዘጋጁ!” የሚል ድንገተኛ ትእዛዝ ተላለፈላቸው።
6ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ሂድ ሁኔታውን ሁሉ እያጠና የሚገልጥልህ ተመልካች መድብ። 7ፈረሰኞች ጥንድ ጥንድ ሆነው ሲጋልቡ፥ የአህያና የግመል ጋላቢዎችንም ቢያይ በጥንቃቄ ይመልከታቸው።”
8ዘብ ጠባቂው “ጌታዬ ሆይ! እኔ በማማዬ ላይ ሆኜ ሌት ከቀን በመጠበቅ ላይ ነኝ” ይላል።
9ጥንድ ጥንድ ሆነው በፈረስ የተቀመጡ ሰዎች እነሆ በድንገት ይመጣሉ፤ ዘብ ጠባቂውም “እነሆ ባቢሎን ወደቀች! የሚሰግዱላቸውም ጣዖቶች ሁሉ ተሰባብረው ወደቁ” የሚል ዜና ያስተላልፋል። #ራዕ. 14፥8፤ 18፥2።
10ሕዝቤ እስራኤል ሆይ! ስንዴ በአውድማ ላይ እንደሚወቃ እናንተም ተወቅታችሁ ነበር፤ አሁን ግን የሠራዊት ጌታ፥ የእስራኤል አምላክ፥ የሰማሁትን የምሥራች ቃል ገለጥሁላችሁ።
ስለ ኤዶም የተነገረ ቃል
11ስለ ኤዶም የተነገረ ቃል ይህ ነው፤ አንድ ሰው ከኤዶም በኩል ሆኖ “ዘብ ጠባቂ ሆይ! ሌሊቱ መቼ ይነጋ ይሆን? ሌሊቱ ሊነጋ ምን ያኽል ጊዜ እንደ ቀረው ንገረኝ” ይላል።
12ዘብ ጠባቂውም “በእርግጥ የሌሊቱ ንጋት እየተቃረበ ነው፤ ነገር ግን ሌሊቱ ተመልሶ ይመጣል፤ እንደገና ጠይቀህ ለመረዳት ብትፈልግ ተመልሰህ ናና ጠይቅ” አለው።
ስለ ዐረብ አገር የተነገረ ቃል
13ስለ ዐረብ አገር የተነገረውም ቃል ይህ ነው፤ ከጭነት ግመሎቻችሁ ጋር በዐረብ በረሓ የምትሰፍሩ እናንተ የደዳን ሕዝብ ሆይ፥ 14ተጠምተው ወደ እናንተ ለሚመጡት ሁሉ ውሃ ስጡአቸው፤ እናንተም የቴማ ሕዝብ ሆይ! ለስደተኞች ምግብ አቅርቡላቸው። 15ሕዝቡ ሁሉ ከሚገደሉበት ሰይፍ፥ ከተደገነባቸው ቀስትና ከጦርነት አደጋ ሁሉ ለማምለጥ በመሸሽ ላይ ናቸው።
16ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የሠራተኞች የሥራ ውል እንደሚያልቅ ልክ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የቄዳር ነገዶች ክብር ይወገዳል፤ 17ከቄዳር አርበኞች የሚተርፉት ቀስተኞች ጥቂቶች ናቸው። እኔ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ