ትንቢተ ሆሴዕ 14
14
ሆሴዕ የእስራኤል ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ መጠየቁ
1የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በኃጢአታችሁ ምክንያት የተሰናከላችሁ ስለ ሆነ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ። 2የኑዛዜ ቃል ይዛችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እንዲህም በሉት፦ “ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር በለን፤ በምሕረት ተቀበለን፤ እኛም የአንደበታችን መልካም ፍሬ የሆነውን ምስጋና እናቀርብልሃለን። 3አሦር አያድነንም፥ በጦር ፈረሶችም አንታመንም፤ ከእንግዲህ ወዲህ በእጃችን የሠራነውን ጣዖት ሁሉ ‘አምላክ’ ብለን አንጠራም፤ አምላክ ሆይ! ወላጆቻቸው የሞቱባቸው በአንተ ምሕረትን ያገኛሉ።”
ለአዲስ ሕይወት ተስፋ መሰጠቱ
4እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የሕዝቤን አለመታመን ፈውሼ፤
ወደ እኔ እመልሳቸዋለሁ
ቊጣዬ ከእነርሱ ስለ ተመለሰ፥
እኔ በገዛ ፈቃዴ እወዳቸዋለሁ፤
5ለእስራኤል ሕዝብ እንደሚወርድ ጠል እሆናለሁ።
እነርሱ እንደ አበባ ይፈካሉ፤
እንደ ሊባኖስ ዛፎችም ሥር ይሰዳሉ።
6ቡቃያዎቻቸው ይለመልማሉ፤
እንደ ወይራ ዛፍ የሚያምሩ ይሆናሉ፤
እንደ ሊባኖስ ደን መልካም መዓዛ ይሰጣሉ።
7ተመልሰውም በእኔ ጥላ ሥር ይሆናሉ፤
እንደ እህል ቡቃያ ይለመልማሉ፤
እንደ ወይን ተክልም ያብባሉ፤
መዓዛቸውም እንደ ሊባኖስ የወይን ጠጅ ዝነኛ ይሆናል።
8የእስራኤል ሕዝብ ሆይ!
እኔ ከጣዖቶች ጋር ምን ግንኙነት አለኝ?
ለጸሎታችሁ መልስ የምሰጥና የምንንከባከባችሁ እኔ ነኝ፤
እኔ ዘወትር ለምለም ሆኖ እንደሚታይ የጥድ ዛፍ ነኝ፤
ፍሬያማ የምትሆኑትም በእኔ አማካይነት ነው።”
መደምደሚያ
9ጥበብ ያላቸው እነዚህን ነገሮች ይረዳሉ፤ አስተዋዮችም ያውቋቸዋል፤ የእግዚአብሔር መንገድ ትክክል ነው፤ ጻድቃን ይሄዱበታል፤ ኃጢአተኞች ግን ይሰናከሉበታል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 14: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997