እንደ ደመና በዙሪያችን የከበቡን እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ስላሉን እኛ እንደ ሸክም የሆነብንን ነገር ሁሉ በእኛ ላይ የተጣበቀብንን ኃጢአት አስወግደን በፊታችንም ያለውን የሩጫ እሽቅድድም በትዕግሥት በመጽናት እንሩጥ። የምንሮጠውም የእምነታችን መሥራችና ፈጻሚ የሆነውን ኢየሱስን በመመልከት ነው፤ እርሱ በፊቱ በተደቀነው ደስታ ምክንያት በመስቀል ላይ የመሞትን ውርደት ከምንም ሳይቈጥር የመስቀልን መከራና ሞት ታገሠ፤ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝም ተቀመጠ። እንግዲህ ሳትሰለቹና ተስፋ ሳትቈርጡ ይህን ሁሉ የኃጢአተኞችን ተቃውሞ የታገሠውን ኢየሱስን ተመልከቱ። እናንተ ከኃጢአት ጋር በመታገል ገና ደም እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም። እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ አድርጎ እንዲህ ሲል የመከራችሁን ረስታችኋል፤ “ልጄ ሆይ! የጌታን ተግሣጽ አታቃል፤ በቀጣህም ጊዜ ተስፋ አትቊረጥ፤ ጌታ የሚወደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጁ አድርጎ የሚያየውንም ይቀጣል።” እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ ስለሚቈጥራችሁ ቅጣትን ታገሡ፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ልጆች የሆኑ ሁሉ የሚቀበሉትን ቅጣት እናንተም ካልተቀበላችሁ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ከዚህም በቀር እኛ ሁላችን የሚቀጡን የሥጋ አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር፤ ታዲያ፥ በሕይወት ለመኖር ለመንፈሳዊ አባታችን በይበልጥ መታዘዝ እንዴት አይገባንም! እነርሱ መልካም መስሎ እንደ ታያቸው ለጥቂት ጊዜ ቀጥተውናል፤ እርሱ ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለጥቅማችን ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ የሚያስደስት አይመስልም፤ በኋላ ግን ለተለማመዱት ሰዎች ሰላም የሞላበትን የጽድቅ ፍሬ ያስገኝላቸዋል። ስለዚህ የዛሉትን እጆቻችሁንና የደከሙትን ጒልበቶቻችሁን አበርቱ። አንካሳ የሆነው እንዲፈወስ እንጂ ከቦታው ወጥቶ እንዳይናጋ ለእግራችሁ የቀና መንገድ አድርጉ።
ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 12 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 12:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos