በመዝሙር የቀረበ የነቢዩ ዕንባቆም ጸሎት ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ! ስላደረግኸው አስደናቂ ሥራ ሁሉ ሰምቼ እጅግ ፈራሁ፤ አሁንም በዘመናችን የቀድሞውን ሥራህን ደግመህ አድርግ፤ በየዘመናቱም እንዲታወቅ አድርግ፤ በምትቈጣበት ጊዜ እንኳ ምሕረትህን አታርቅ። እግዚአብሔር በቅድስናው ከቴማን አገርና፥ ከፋራን ተራራ እንደገና ይመጣል፤ መለኮታዊ ክብሩ ሰማያትን ሸፍኖአል፤ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል። ብርሃኑ እንደ ፀሐይ ብርሃን ነው ኀይሉን ከሸፈነው እጁም የብርሃን ጮራ ይወጣል፤ ቸነፈር ፊት ፊቱ ይሄዳል፤ መቅሠፍትም ከኋላው ይከተለዋል። እርሱ ሲቆም ምድር ትናወጣለች፤ እርሱ ሲመለከታቸው ሕዝቦች ይንቀጠቀጣሉ፤ የጥንቱ ተራራዎች ይናዳሉ፤ ከጥንት ጀምሮ የእርሱ መረማመጃ የነበሩት ኰረብቶች ወደ ታች ይሰጥማሉ። የኢትዮጵያ ሰፈር ሲጨነቅ፥ የምድያምም ሰዎች ሲንቀጠቀጡ አየሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ፈረሶችህንና ሠረገላዎችህን ወደ ድል በመራኸቸው ጊዜ፥ ኀይለኛው ቊጣህ በወንዞች ላይ ነበርን? ወይስ በባሕሩ ላይ ተቈጥተህ ነበርን? ቀስትህን ከሰገባው አወጣህ፤ ፍላጻህንም ለመወርወር አነጣጠርህ፤ ምድሪቱንም ሰንጥቀህ ወንዞች አስገኘህ። ተራራዎች አንተን አይተው በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤ የዝናብም ጐርፍ ምድርን እየጠራረገ አለፈ፤ ውቅያኖስ ከፍተኛ ድምፅ አሰማ፤ ማዕበሉም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለ። እንደ ፍላጻ ከሚወረወረውና እንደ ጦር ከሚያንጸባርቀው መብረቅህ የተነሣ ፀሐይና ጨረቃ በየቦታቸው ቆሙ። በምድር ላይ ቆምክ፤ በቊጣህም ሕዝቦችን ረጋገጥካቸው። ሕዝብህን ለመታደግ፥ ቀብተህ ያነገሥከውንም ንጉሥ ለማዳን ወጣህ፤ የጥፋት አገር መሪ የሆነውን ቀጠቀጥከው፤ ተከታዮቹንም አጥፍተህ እርቃኑን አስቀረኸው። ከእግር እስከ ራሱም አራቈትከው። እኛን ለመበታተን እንደ ዐውሎ ነፋስ የመጣውን የጦረኞቹን አለቃ በገዛ ቀስቱ ወጋኸው። ደካማ እንስሶችን ለመቦጨቅ እንደሚጓጓ አውሬ እርሱም የተደበቁትን ድኾች ለማጥቃት የተዘጋጀ ነበር። አንተ ባሕሩን በፈረሶችህ በምትረጋግጥበት ጊዜ ጥልቁ ባሕር ይናወጣል። ይህን ሁሉ ስሰማ ሰውነቴ ይርበደበዳል፤ ድምፁም ከንፈሮቼን ያንቀጠቅጣል፤ አጥንቶቼ ይበሰብሳሉ፤ እግሮቼ ከታች ይብረከረካሉ፤ በጠላቶቻችን ላይ መከራ የሚደርስበትን ጊዜ በትዕግሥት እጠባበቃለሁ። ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያብብ፥ በወይን ተክል ላይም ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ዛፍም ምንም ፍሬ ባይሰጥ፥ በእርሻዎች ላይ ሰብል ቢጠፋ፥ የበግ መንጋዎች ሁሉ ቢያልቁ፥ በበረት ውስጥ ምንም ከብት ባይገኝ፥ ይህም ሁሉ ቢሆን፥ እኔ በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በአምላኬ፥ በመድኃኒቴ ሐሤት አደርጋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር ብርታቴ ነው፤ እግሮቼንም እንደ ዋልያ እግሮች ያጠነክርልኛል፤ በተራሮችም ላይ እንድራመድ ያደርገኛል።
ትንቢተ ዕንባቆም 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ዕንባቆም 3:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች