ትንቢተ ዕንባቆም 2

2
እግዚአብሔር ለዕንባቆም የሰጠው መልስ
1በጥበቃ ቦታዬ እቆማለሁ በግንቡ ጫፍ ላይም ቦታዬን እይዛለሁ፤ እግዚአብሔር ምን እንደሚለኝ ለጥያቄዬም ምን መልስ እንደሚሰጥ እጠባበቃለሁ።
2እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፦ “የምገልጥልህን ራእይ ጻፍ፤ በቀላሉ እንዲነበብም አድርገህ በሰሌዳ ላይ ቅረጸው፤ 3ምክንያቱም ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ይጠብቃል፤ እርሱም የሚናገረው የሚፈጸምበትን ቀን ነው፤ ሐሰትም የለበትም፤ ጊዜ የሚወስድ ቢመስልም ጠብቅ፤ በእርግጥ ይደርሳል፤ አይዘገይምም። #ዕብ. 10፥37። 4ትዕቢተኞችን ተመልከት፤ አስተሳሰባቸው ቅን አይደለም፤ ጻድቃን ግን በእምነታቸው ይኖራሉ።” #ሮም 1፥17፤ ገላ. 3፥11፤ ዕብ. 10፥38።
የክፉ ሰዎች አወዳደቅ
5በእርግጥ ሀብት ሰውን ያታልላል፤ ትምክሕተኛ ሰው ዕረፍት የለውም፤ እንደ መቃብር ስስታም እንደ ሞትም በቃኝ የማይል ስለ ሆነ መንግሥታትን ሁሉ ለራሱ ይወራል፤ ሕዝቦችንም ይማርካል። #2፥5 ሀብት፦ አንዳንድ የዕብራይስጥ ቅጂዎች “ሀብት” ሲሉ፥ ሌሎች “የወይን ጠጅ” የሚሉም አሉ። 6ሰው ሁሉ እንደነዚህ ባሉት ሰዎች ላይ በመሳለቂያ እንቆቅልሽ እንዲህ ይላል፦ “ያንተ ያልሆነውን የምታግበሰብስ ወዮልህ! በመያዣነት በተወሰዱ ዕቃ ራስህን የምታበለጽገው እስከ መቼ ነው?”
7ባለ ዕዳዎቻችሁ በድንገት አይነሡምን? ተነሥተውስ አያርበደብዱአችሁምን? ከዚያ በኋላ እናንተ የእነርሱ ምርኮኞች ትሆናላችሁ። 8የብዙ ሕዝቦችን ንብረት ስለ ዘረፋችሁ ከእነርሱ የተረፉት የእናንተን ንብረት ይዘርፋሉ፤ ይህም የሚሆነው እናንተ ሰዎችን ስለ ገደላችሁ፥ ምድሪቱን ከተሞችንና በእነርሱ የሚኖሩትን ስላጠፋችሁ ነው። 9አደጋ እንዳይደርስበት መኖሪያውን ከፍ ባለ አምባ ላይ የሚመሠርትና በሕገ ወጥ ገቢ ቤቱን ለሚሠራ ወዮለት! 10ተንኰልን ዐቅደህ ብዙ ሰዎችን በመግደል በቤትህ ኀፍረትን አምጥተሃል፤ ሕይወትህንም ለአደጋ አጋልጠሃል። 11የግንቡ ድንጋዮች ከግድግዳው ይጮኻሉ፤ የእንጨት ምሰሶችም ይህንኑ ከውስጥ ያስተጋባሉ። 12ሰውን በመግደል ከተማን ለምትቈረቊሩና፥ በበደል ዋና ከተማን ለምትሠሩ ወዮላችሁ! 13ሰዎች የሚሠሩት ለቃጠሎ፥ መንግሥታትም የሚደክሙት ምንም ጥቅም ለሌለው ነገር እንዲሆን የሚያደርግ የሠራዊት አምላክ አይደለምን? 14ባሕር በውሃ የተሞላ እንደ ሆነ ሁሉ፥ ምድርም የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ የተሞላች ትሆናለች። #ኢሳ. 11፥9። 15ኀፍረተ ሥጋው ሲገለጥ ለማየት ለሰው ቊጣህን እንደ ጠንካራ መጠጥ የምትሰጥና እስኪሰክርም ድረስ የምታጠጣው አንተ ሰው ወዮልህ! 16አንተ ራስህ ጠጥተህ በመስከር ትንገዳገዳለህ፤ አንተም በተራህ በክብር ፈንታ ውርደትን ትለብሳለህ፤ እግዚአብሔር ኀይለኛ የቅጣት ጽዋ እንድትጠጣ ያደርግሃል፤ ክብርህን ወደ ውርደት ይለውጣል። 17በሊባኖስ ላይ ያደረስከው ዐመፅ ይደርስብሃል፤ በእንስሶች ላይ ያደረግኸው ጥፋት ያስደነግጥሃል፤ ይህም የሚሆነው ሰውን ስለ ገደልክ፥ አገሮችንና ከተሞችን፥ በእነርሱም ውስጥ ያለውን ሁሉ ስላጠፋህ ነው። 18ኧረ ለመሆኑ የጣዖት ጥቅሙ ምንድን ነው? እርሱ እኮ በሰው እጅ ተቀርጾ የተሠራ ነገር ነው፤ ከሐሰት በቀር ከእርሱ ምንም አይገኝም፤ ታዲያ እርሱን ቀርጾ የሠራው ሰው ምንም መናገር በማይችል በዚህ ጣዖት መታመኑ ምን ሊጠቅመው ነው? 19ከእንጨት ተጠርቦ የተሠራውን ነገር “ንቃ!” ከድንጋይ ተቀርጾ የተሠራውንም ነገር “ተነሥ!” ለምትል ለአንተ ወዮልህ! ለመሆኑ ጣዖት አንዳች ምሥጢር ሊገልጥልህ ይችላልን? እነሆ ጣዖት በብርና በወርቅ ተለብጦ የተሠራ ነው፤ የሕይወት እስትንፋስ ግን ፈጽሞ የለውም።
20እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ስለዚህ የዓለም ሕዝብ ሁሉ በፊቱ ጸጥ ይበል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ