የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 9:1-29

ኦሪት ዘፍጥረት 9:1-29 አማ05

እግዚአብሔር ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ብዙ፥ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት፤ እንስሶች፥ ወፎች፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና ዓሣዎች ሁሉ እናንተን በመፍራትና በመደንገጥ ይኑሩ፤ ሁሉም በሥልጣናችሁ ሥር ይሁኑ። ከዚህ በፊት የአትክልት ዐይነቶችን ምግብ አድርጌ እንደሰጠኋችሁ እነዚህንም ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች ሁሉ ምግብ እንዲሆኑአችሁ ሰጥቻችኋለሁ። ነገር ግን በደሙ ውስጥ ሕይወት ስላለ ደም ያለበትን ሥጋ አትብሉ። ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ በተጠያቂነት ላይ እሻዋለሁ፤ ከእንስሶች ሁሉና ከሰውም ላይ እሻዋለሁ፤ ከሰው ሁሉ የሰውን ሕይወት እሻዋለሁ። ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳያ ስለ ሆነ፥ ሰውን የሚገድል ሁሉ በሰው እጅ ይሞታል። “እናንተ ፍሬያማ ሆናችሁ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፥ ከእናንተና ከዘራችሁ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ እንዲሁም ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሁሉ፥ ማለትም ከወፎች፥ ከእንስሶችና ከአራዊት፥ ከአንተ ጋር ከመርከቡ ውስጥ ከወጡት ፍጥረቶችና ዘሮቻቸው ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ በዚህም በገባሁላችሁ ቃል ኪዳን መሠረት፥ ከእንግዲህ ወዲህ ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ በጥፋት ውሃ ከቶ አይደመሰሱም፤ ምድርም ዳግመኛ በጥፋት ውሃ አትጠፋም።” እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፦ “ከእናንተና ከሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ጋር ለምገባው ለዚህ ለዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ምልክት ይሆን ዘንድ፥ ቀስቴን በደመናዎች ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም ቀስት ከምድር ጋር ለገባሁት ቃል ኪዳን ምልክት ሆኖ ይኖራል። ሰማይን በደመና በምሸፍንበትና ቀስትም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ፥ ‘ከእንግዲህ ወዲህ የጥፋት ውሃ፤ ሕያዋን ፍጥረቶችን ሁሉ ከቶ አያጠፋም’ ብዬ ከእናንተና ከሌሎች ሕያዋን ፍጥረቶች ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ። ቀስት በደመናዎች ላይ በሚታይበት ጊዜ ተመልክቼ በእኔና በምድር ላይ ባሉት ሕይወት ባላቸው ፍጥረቶች መካከል ያለውን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ።” እግዚአብሔርም ኖኅን እንዲህ አለው፦ “ይህ ቀስት በምድር ላይ በእኔና ሕይወት ባላቸው ፍጥረቶች ሁሉ መካከል የገባሁትን ቃል ኪዳን የሚያስታውስ ምልክት ነው።” ከመርከቡ የወጡት የኖኅ ልጆች ሴም፥ ካምና ያፌት ናቸው፤ ካም የከነዓን አባት ነው፤ አሁን በምድር ላይ ተበትነው ያሉት ሰዎች ሁሉ የተገኙት ከእነዚህ ከሦስቱ የኖኅ ልጆች ነው። ኖኅ ገበሬ ነበረ፤ የወይን ተክልንም መትከል ጀመረ፤ ከዕለታት አንድ ቀን ኖኅ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ሰከረ፤ ልብሱንም አውልቆ ራቊቱን በድንኳን ውስጥ ተኛ። የከነዓን አባት የሆነው ካም፥ አባቱ ኖኅ እራቁቱን እንደ ሆነ ባየ ጊዜ ወደ ውጪ ወጥቶ፥ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። ሴምና ያፌትም ልብስ በስተኋላቸው፥ በትከሻቸው ያዙ፤ ወደ ድንኳኑም የኋሊት ሄዱና የአባታቸውን ራቊትነት እንዳያዩ ፊታቸውን አዙረው ራቊትነቱን ሸፈኑ፤ የአባታቸውንም ራቊትነት ኣላዩም። ኖኅ ስካሩ አልፎለት ሲነቃ፥ ትንሹ ልጁ ያደረገበትን ዐወቀ፤ እንዲህም አለ፤ “ከነዓን የተረገመ ይሁን! ለወንድሞቹ የአገልጋዮች አገልጋይ ይሁን፤ እንደገናም እንዲህ አለ፤ የሴም አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን! ከነዓንም የሴም አገልጋይ ይሁን! እግዚአብሔር የያፌትን ምድር ያስፋ! የያፌት ዘሮች ከሴም ዘሮች ጋር አብረው ይኑሩ! ከነዓን የያፌት አገልጋይ ይሁን።” ከጥፋት ውሃ በኋላ ኖኅ 350 ዓመት ኖረ። ዕድሜውም 950 ዓመት ሲሆነው ሞተ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}