የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 7:11-24

ኦሪት ዘፍጥረት 7:11-24 አማ05

ኖኅ 600 ዓመት በሆነው ጊዜ፥ በሁለተኛው ወር በዐሥራ ሰባተኛው ቀን ላይ ከምድር በታች ያለው የታላቁ ውሃ ምንጮች ሁሉ በድንገት ተነደሉ፤ በሰማይ ያሉት የውሃ መስኮቶች ሁሉ ተከፈቱ። ዝናብም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዘነበ። ዝናቡ መዝነብ በጀመረበት ቀን፥ ኖኅና ሚስቱ ከልጆቻቸው ከሴም፥ ከካም፥ ከያፌትና ከሦስቱም ልጆቻቸው ሚስቶች ጋር ወደ መርከቡ ገቡ። ከአራዊት፥ ከእንስሶች፥ በደረታቸው እየተሳቡ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና በሰማይ ከሚበርሩ ወፎች ከእያንዳንዱ ዐይነት አብረዋቸው ገቡ። በዚህ ዐይነት እስትንፋስ ካላቸው ፍጥረቶች ከእያንዳንዱ ዐይነት ሁለት ሁለት እየሆኑ ከኖኅ ጋር ወደ መርከቡ ገቡ፤ ፍጥረት ሁሉ ወንድና ሴት ሆነው ወደ መርከቡ የገቡት እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ነው፤ ከዚህ ቀጥሎ እግዚአብሔር ከኖኅ በስተኋላ የመርከቡን በር ዘጋ። የጥፋት ውሃ አርባ ቀን ድረስ በመዝነብ እየበረታ ሄደ፤ የውሃውም ጥልቀት እየጨመረ ስለ ሄደ መርከቡን ከምድር በላይ ከፍ አደረገው፤ ውሃ በምድር ላይ እያደገና እየበረታ በሄደ መጠን መርከቡ በውሃው ላይ መንሳፈፍ ጀመረ። ውሃውም ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራራዎችን እንኳ እስከሚሸፍን ድረስ ጥልቅ ሆነ። ውሃው ከተራሮች ጫፍ በላይ ሰባት ሜትር ያኽል ከፍ አለ። ወፎችና እንስሶች፥ አራዊት፥ ሰዎችም ሁሉ ሳይቀሩ ሞቱ። በምድር ላይ ያሉት ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች ሁሉ ጠፉ። በምድር ላይ የሚኖር እስትንፋስ ያለው ነገር ሁሉ ሞተ። እግዚአብሔር በምድር ላይ ያለውን ሕያው ፍጥረት ሁሉ፥ ሰዎችንም፥ እንስሶችንም፥ ወፎችንም፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሳይቀሩ ሁሉንም አጠፋ። ከሞት የተረፉት ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩት ብቻ ነበሩ። ውሃው እስከ መቶ ኀምሳ ቀን አልጐደለም ነበር።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}