የአዳም የዘር ሐረግ ከዚህ የሚከተለው ነው፦ እግዚአብሔር ሰውን በፈጠረ ጊዜ በራሱ አምሳያ ፈጠራቸው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ ባረካቸው፤ “ሰው” ብሎም ሰየማቸው። አዳም መቶ ሠላሳ ዓመት በሆነው ጊዜ በመልኩና በአምሳያው እርሱን የሚመስል ወንድ ልጅ ወለደ፤ “ሤት” የሚል ስምም አወጣለት። ከዚህ በኋላ አዳም 800 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ፤ ዕድሜው 930 ዓመት ሲሆነውም ሞተ። ሴት 105 ዓመት ሲሆነው ሄኖስን ወለደ፤ ከዚህ በኋላ ሴት 807 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ፤ ዕድሜው 912 ዓመት ሲሆነውም ሞተ። ሄኖስ 90 ዓመት ሲሆነው ቃይናንን ወለደ፤ ከዚህ በኋላ 815 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ፤ ዕድሜው 905 ሲሆነውም ሞተ። ቃይናንም 70 ዓመት ሲሆነው መላልኤልን ወለደ፤ ከዚህ በኋላ 840 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ፤ ዕድሜው 910 ሲሆነውም ሞተ። መላልኤል 65 ዓመት ሲሆነው ያሬድን ወለደ፤ ከዚህ በኋላ 830 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችን ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ፤ ዕድሜው 895 ሲሆነውም ሞተ። ያሬድ 162 ዓመት ሲሆነው ሔኖክን ወለደ፤ ከዚህ በኋላ 800 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ፤ ዕድሜው 962 ሲሆነውም ሞተ። ሔኖክ 65 ዓመት ሲሆነው ማቱሳላን ወለደ፤ ከዚህ በኋላ ሔኖክ የእግዚአብሔርን መንገድ በመከተል 300 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ፤ ዕድሜው 365 እስኪሆነው ድረስ ኖረ፤ ይህን ያኽል ዘመን የኖረውም የእግዚአብሔርን መንገድ በመከተል ነበር፤ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ስለ ወሰደው አልተገኘም። ማቱሳላ 187 ዓመት ሲሆነው ላሜክን ወለደ፤ ከዚህ በኋላ 782 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ፤ ዕድሜው 969 ሲሆነውም ሞተ። ላሜክ 182 ዓመት ሲሆነው ወንድ ልጅ ወለደ፤ “ይህ ልጅ እግዚአብሔር በረገማት ምድር ላይ ከብርቱ ሥራችን ያሳርፈናል” ሲል “ኖኅ” ብሎ ጠራው። ከዚህ በኋላ ላሜክ 595 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ፤ ዕድሜው 777 ሲሆነውም ሞተ። ኖኅ 500 ዓመት ከሆነው በኋላ ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደ፤ እነርሱም ሴም፥ ካምና ያፌት ይባሉ ነበር።
ኦሪት ዘፍጥረት 5 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 5:1-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos