ኦሪት ዘፍጥረት 45:1-28

ኦሪት ዘፍጥረት 45:1-28 አማ05

ዮሴፍ የናፍቆት ስሜቱን በአገልጋዮቹ ፊት መቈጣጠር ባለመቻሉ “ሁላችሁም ከዚህ ውጡ” ብሎ አዘዘ፤ ስለዚህ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ በገለጠ ጊዜ ማንም የውጪ ሰው በአጠገቡ አልነበረም። በዚህ ጊዜ ግብጻውያን እስኪሰሙት ድረስ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ የፈርዖንም ቤተሰብ ወሬውን ሰማ። ዮሴፍ ወንድሞቹን “እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወት አለን?” አላቸው። ወንድሞቹ የተናገረውን በሰሙ ጊዜ እጅግ ደነገጡ፤ መልስ መስጠትም ተሳናቸው። በዚህ ጊዜ ዮሴፍ “እስቲ ወደ እኔ ቀረብ በሉ” አላቸው፦ ከቀረቡም በኋላ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ፤ ነገር ግን ይህን በማድረጋችሁ በመጸጸት አትበሳጩ፤ እግዚአብሔር እኔን አስቀድሞ የላከኝ የሰዎችን ሕይወት እንዳተርፍ ነው። በምድር ላይ ራብ ከገባ ሁለተኛ ዓመቱን ይዞአል፤ ሰዎች አርሰው መከር መሰብሰብ የማይችሉባቸው አምስት ዓመቶች ገና ይመጣሉ። እግዚአብሔር አስቀድሞ ወደዚህ የላከኝ በዚህ በአስደናቂ ዘዴ የእናንተን ሕይወት በማዳን በምድር ላይ ዘር እንዲቀርላችሁ አስቦ ነው። “ስለዚህ ወደዚህ የላከኝ ራሱ እግዚአብሔር እንጂ እናንተ አይደላችሁም፤ እግዚአብሔር ለፈርዖን እንደ መካሪ አባት፥ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታና የመላው ግብጽ አገር ገዢ አደረገኝ። አሁን በፍጥነት ተመልሳችሁ ወደ አባቴ ሂዱና ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይልሃል በሉት፤ ‘እግዚአብሔር የመላው ግብጽ ገዢ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና፤ ልጆችህን፥ የልጅ ልጆችህን፥ በጎችህን፥ ፍየሎችህን፥ ከብቶችህን ሌላም ያለህን ነገር ሁሉ ይዘህ ና፥ በእኔው አቅራቢያ በሚገኘው በጌሴም ምድር ትኖራለህ። አምስት የራብ ዓመቶች ገና ስለሚቀሩ አንተና ቤተሰብህ እንስሶችህም ጭምር ራብ እንዳይደርስባችሁ በጌሴም እመግብሃለሁ።’ ” ቀጥሎም ዮሴፍ እንዲህ አለ፤ “አሁን የምናገራችሁ እኔ ዮሴፍ መሆኔን እናንተና አንተም ወንድሜ ብንያም አይታችሁ ለማረጋገጥ ችላችኋል፤ በግብጽ አገር ያለኝን ታላቅ ክብርና ያያችሁትንም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፤ በፍጥነትም ወደዚህ አምጡት።” ከዚህ በኋላ የወንድሙን የብንያምን አንገት ዐቅፎ አለቀሰ፤ ብንያምም ወንድሙን ዐቅፎ አለቀሰ፤ ዮሴፍ የቀሩትንም ወንድሞቹን አንድ ባንድ እየሳመ አለቀሰ፤ ከዚህ በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር መነጋገር ጀመሩ። የዮሴፍ ወንድሞች መምጣት በፈርዖን ቤተ መንግሥት በተሰማ ጊዜ ፈርዖንና ባለሥልጣኖቹ ደስ አላቸው፤ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “ወንድሞችህ አህዮቻቸውን ጭነው ወደ ከነዓን እንዲመለሱ ንገራቸው፤ አባታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ይምጡ፤ እኔም በግብጽ አገር ለም የሆነውን ቦታ መርጬ እሰጣቸዋለሁ፤ በቂ ምግብ አግኝተው በደስታ መኖር ይችላሉ። እንዲሁም ሚስቶቻቸውን፥ ልጆቻቸውንና አባታቸውን አሳፍረው የሚያመጡበት ከግብጽ አገር ሠረገሎችን ይዘው እንዲሄዱ እዘዛቸው። በግብጽ ምድር ለም የሆነውን ቦታ ስለሚያገኙ ቤት ንብረታቸውን ትተው በመምጣታቸው ቅር አይሰኙ።” የያዕቆብ ልጆች ልክ እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ ዮሴፍም በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ሠረገሎችንና ለጒዞ የሚሆናቸውን ስንቅ ሰጣቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም አንድ አንድ የክት ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን አምስት የክት ልብስና ሦስት መቶ ብር ሰጠው። ለአባቱም በዐሥር አህዮች የተጫነ ከግብጽ ምድር የሚገኘውን መልካም ነገር ሁሉ ላከለት፤ እንዲሁም በሚመጣበት ጊዜ ለስንቅ የሚሆነው በሌሎች ዐሥር እንስት አህዮች የተጫነ እህል፥ ዳቦና ሌላም ምግብ ላከለት። በዚህ ሁኔታ ወንድሞቹን ካሰናበታቸው በኋላ “በመንገድ አትጣሉ” ብሎ መከራቸው። የዮሴፍ ወንድሞች ከግብጽ ተነሥተው በከነዓን ወደሚኖረው አባታቸው ወደ ያዕቆብ ተመለሱ። እዚያም እንደ ደረሱ አባታቸውን “ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በመላው ግብጽ ላይ አስተዳዳሪ ሆኖአል” አሉት። ያዕቆብ ግን እጅግ ደነገጠ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም። ነገር ግን ዮሴፍ ያላቸውን ሁሉ በነገሩት ጊዜና እርሱን ወደ ግብጽ የሚወስዱበትን ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላ ባየ ጊዜ ሕይወቱ በደስታ ታደሰ፤ ከዚህ በኋላ ያዕቆብ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት መኖሩን ካረጋገጥሁ ይበቃኛል፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ አየዋለሁ” አለ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}