ኦሪት ዘፍጥረት 44
44
ጠፋ የተባለው ዋንጫ በብንያም ስልቻ ውስጥ መገኘቱ
1ዮሴፍ የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘው፤ “ለመጫን የሚችሉትን ያኽል በየስልቻዎቻቸው ሙላላቸው፤ የእያንዳንዱንም ገንዘብ በየስልቻው አፍ አስቀምጠው። 2የእኔን የብር ዋንጫ ውሰድና በታናሽ ወንድማቸው ስልቻ ውስጥ እህል ለመሸመት ከመጣው ገንዘብ ጋር ክተተው።” የቤቱም አዛዥ ዮሴፍ እንደ ነገረው አደረገ።
3ጠዋት በማለዳ ወንድማማቾቹ አህዮቻቸውን ይዘው እንዲሄዱ ተደረገ። 4ከከተማው ወጥተው ገና ጥቂት መንገድ ርቀው እንደ ሄዱ፥ ዮሴፍ የቤቱን አዛዥ እንዲህ አለው፤ “እነዚያን ሰዎች ተከታትለህ ያዛቸው፤ ወደ እነርሱም ስትደርስ ‘በመልካም ፈንታ ክፉ የመለሳችሁት ስለምንድን ነው? 5የጌታዬን የብር ዋንጫ የሰረቃችሁት ለምንድን ነው? ዋንጫው ጌታዬ የሚጠጣበትና ሁሉን ነገር መርምሮ የሚያውቅበት እንደ ሆነ አታውቁምን? ይህ ያደረሳችሁት በደል እጅግ ከባድ ነው’ ብለህ ንገራቸው።”
6የቤቱም አዛዥ ወደ ሰዎቹ እንደ ደረሰ ልክ እንደ ተባለው ነገራቸው፤ 7እነርሱም እንዲህ በማለት መልስ ሰጡት፤ “ጌታችን ሆይ፤ እንዴት እንዲህ ትናገራለህ? እኛ ይህን የመሰለ ነገር እንዳላደረግን በመሐላ እናረጋግጣለን፤ 8ከአሁን ቀደም በየስልቻችን ያገኘነውን ገንዘብ እንኳ ከከነዓን መልሰን እንዳመጣንልህ ታውቃለህ፤ ታዲያ አሁን ከጌታህ ቤት ብርም ሆነ ወርቅ የምንሰርቀው ለምንድን ነው? 9ከእኛ አንዱ ይህን ዕቃ ይዞ ቢገኝ በሞት ይቀጣ፤ የቀረነውም የአንተ ባሪያዎች እንሁን።”
10እርሱም “መልካም ነው፤ እናንተ ባላችሁት እስማማለሁ፤ ሆኖም ዋንጫውን የወሰደው ሰው ብቻ የእኔ ባሪያ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን በነጻ ልትሄዱ ትችላላችሁ” አላቸው። 11ስለዚህ በፍጥነት ስልቻዎቻቸውን አወረዱ፤ እያንዳንዱም የራሱን ስልቻ ከፈተ። 12የዮሴፍ አገልጋይ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ የሁሉንም ስልቻ በተራ በመበርበር ዋንጫውን በጥንቃቄ ፈለገ፤ በመጨረሻ ግን ዋንጫው በብንያም ስልቻ ውስጥ ተገኘ። 13ወንድማማቾቹ ይህን ባዩ ጊዜ በሐዘን ልብሶቻቸውን ቀደዱ፤ ስልቻዎቻቸውንም ጭነው ወደ ከተማ ተመለሱ።
14ይሁዳና ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ሲመጡ ገና በቤት ሳለ አገኙት፤ ወደ መሬት ጐንበስ ብለው እጅ ነሡት፤ 15ዮሴፍም “ይህ ያደረጋችኹት ነገር ምንድን ነው? እኔ ባለሁበት ደረጃ የሚገኝ ሰው በተለየ ጥበብ ሁሉን ነገር መርምሮ ማወቅ የማይችል መሰላችሁን?”
16ይሁዳም “እንግዲህ ለጌታችን ምን መልስ እንሰጣለን? ራሳችንን ነጻ የምናደርግበት መልስ መስጠት ከቶ አንችልም፤ እግዚአብሔር የሠራነውን በደል ገልጦታል፤ እንግዲህ ዋንጫው የተገኘበት ሰው ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ባሪያዎችህ እንሁን” አለ።
17ዮሴፍም “ይህንንስ ከቶ አላደርገውም! ዋንጫው የተገኘበት ሰው ብቻ የእኔ ባሪያ መሆን አለበት፤ ሌሎቻችሁ በሰላም ወደ አባታችሁ መመለስ ትችላላችሁ!” አለ።
ይሁዳ ስለ ብንያም ዮሴፍን መለመኑ
18ይሁዳ ወደ ዮሴፍ ቀርቦ እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ ሆይ፤ እባክህ አንድ ቃል እንድናገር ፍቀድልኝ፤ ምንም እንኳ የፈርዖንን ያኽል የተከበርክ ብትሆን እባክህ አትቈጣኝ። 19ጌታዬ ከአሁን ቀደም ‘አባት አላችሁ ወይ? ሌላ ወንድምስ አላችሁ ወይ?’ ብለህ ጠየቅከን፤ 20እኛም ‘ሽማግሌ አባት አለን፤ በስተርጅና የወለደውም ታናሽ ወንድም አለን፤ የልጁ ወንድም ሞቶአል፤ ከእናቱ ልጆች የቀረው እርሱ ብቻ ስለ ሆነ አባቱ በጣም ይወደዋል’ ብለንህ ነበር፤ 21አንተም ‘አየው ዘንድ ይዛችሁልኝ እንድትመጡ’ አልከን፤ 22እኛም ‘ልጁ አባቱን ትቶ መምጣት አይችልም፤ ትቶ ከመጣ ግን አባትየው መሞቱ የማይቀር ነው’ ብለን ለአንተ ለጌታችን ነግረንህ ነበር። 23ጌታችንም ለአንተ ለጌታችን ነግረንህ አገልጋዮቹን ‘ታናሽ ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ በፊቴ አትቀርቡም’ ብለህ በብርቱ አስጠነቀቅከን።
24“እኛም ወደ አባታችን በተመለስን ጊዜ ያልከንን ሁሉ ነገርነው፤ 25ከዚህ በኋላ እርሱ ‘አሁንም ወደ ግብጽ ተመለሱና ጥቂት እህል ሸምቱልን’ አለን። 26እኛም ‘ታናሽ ወንድማችን ከእኛ ጋር ካልሆነ በሰውየው ፊት መቅረብ አንችልም፤ ስለዚህ ወደዚያ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን ከእኛ ጋር የሄደ እንደሆን ብቻ ነው’ አልነው። 27አባታችንም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ራሔል ሁለት ወንዶች ልጆች ብቻ እንደ ወለደችልኝ ታውቃላችሁ። 28ከእነርሱ አንዱ ከአሁን በፊት ተለይቶኛል፤ ከተለየኝ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስላላየሁት ክፉ አውሬ በልቶት ይሆናል፤ 29አሁን ደግሞ ይህንን ወስዳችሁ በእርሱ ላይ አደጋ ቢደርስበት በእርጅናዬ ዘመን የምታመጡብኝ ሐዘን ወደ መቃብር ያወርደኛል።’
30“አሁንም ብላቴናው ከእኛ ተለይቶ በመቅረት ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብንመለስ የብላቴናው ነፍስ ከእርሱ ጋር የታሰረች ስለ ሆነ፥ 31ብላቴናው ከእኛ ጋር እንደሌለ ሲያይ ይሞታል፤ እኛ አገልጋዮችህም የአገልጋይህን የአባታችንን ሽበት በሐዘን ወደ መቃብር እናወርዳለን፤ 32ከዚህም በላይ ስለ ልጁ ደኅንነት ራሴን ዋስ አድርጌ ለአባቴ ሰጥቼአለሁ፤ ደግሞም ‘ልጁን በደኅና መልሼ ባላመጣው በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ተወቃሽ ልሁን’ ብዬ ቃል ገብቼለታለሁ።
33“ስለዚህ እኔ በልጁ ፈንታ የአንተ የጌታዬ ባሪያ ሆኜ እዚሁ ልቅር፤ ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋር ይመለስ፥ 34ልጁን ሳልይዝ እንዴት ወደ አባቴ መመለስ እችላለሁ? ይህን የመሰለ ከባድ ሥቃይ በአባቴ ላይ ሲደርስ ማየት አልችልም።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 44: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997