በሰባቱ የጥጋብ ዓመቶች ምድሪቱ እጅግ ብዙ ሰብል ሰጠች። በግብጽ አገር በእነዚያ ሰባት የጥጋብ ዓመቶች የተገኘውን ሰብል ሰብስቦ በየከተሞች አከማቸ፤ በየእያንዳንዱ ከተማ ያከማቸው እህል በዙሪያው ከሚገኙት እርሻዎች የተመረተ ነበር። በዚህ ዐይነት ዮሴፍ ብዛቱ እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የሆነ እጅግ ብዙ እህል አከማቸ፤ እህሉ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሣ እየሰፈረ መጠኑን ለማወቅ የነበረውን ዕቅድ ተወ። ሰባቱ የራብ ዓመቶች ከመጀመራቸው በፊት፥ ዮሴፍ ከጶጢፌራ ልጅ ከአስናት ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ጶጢፌራ ኦን ተብሎ በሚጠራው ከተማ ካህን ነበረ። ዮሴፍ “እግዚአብሔር የደረሰብኝን መከራና ዘመዶቼን እንድረሳ አደረገኝ” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ምናሴ ብሎ ጠራው፤ እንዲሁም “መከራ በተቀበልኩበት ምድር እግዚአብሔር ልጆች ሰጠኝ” በማለት ሁለተኛውን ልጅ ኤፍሬም ብሎ ጠራው። በግብጽ ምድር ጥጋብ የበዛባቸው ሰባቱ ዓመቶች ተፈጸሙ፤ ዮሴፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረው፥ ሰባቱ የራብ ዓመቶች መግባት ጀመሩ፤ በሌሎች አገሮች ሁሉ ራብ ሆነ፤ ይሁን እንጂ በመላው የግብጽ ምድር በቂ ምግብ ነበር። ራብ በመላው ግብጽ ምድር እየተስፋፋ በሄደ ጊዜ፥ ሕዝቡ ወደ ፈርዖን ሄዶ “ምግብ ስጠን!” ብሎ ጮኸ። ፈርዖንም “ወደ ዮሴፍ ሂዱና እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” ብሎ አዘዛቸው። ራቡ በመላው ግብጽ እየተስፋፋና እየበረታ ስለ ሄደ፥ ዮሴፍ ጐተራዎቹ ሁሉ ተከፍተው እህሉ ለግብጻውያን እንዲሸጥላቸው አደረገ። በዓለም ላይ ራብ ጸንቶ ስለ ነበር የልዩ ልዩ አገር ሕዝቦች ከዮሴፍ እህል ለመግዛት ወደ ግብጽ አገር መጡ።
ኦሪት ዘፍጥረት 41 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 41:47-57
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos