ከሁለት ዓመት በኋላ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ሕልም አየ፤ እርሱ በሕልሙ በዓባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤ ሰባት የወፈሩና የሰቡ ላሞች ከወንዙ ወጥተው ሣር ሲበሉ አየ፤ ቀጥሎም አጥንታቸው እስከሚታይ የከሱ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወንዙ ዳር ከነበሩት ላሞች አጠገብ ቆሙ። የከሱት ላሞች የወፈሩትን ላሞች ዋጡአቸው፤ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ከእንቅልፉ ነቃ። ተመልሶም እንቅልፍ በወሰደው ጊዜ እንደገና ሌላ ሕልም አየ፤ በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ ሰባት የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች አየ፤ ቀጥሎም የቀጨጩና ከበረሓ በተነሣ የምሥራቅ ነፋስ ተመተው የሰለቱ ሰባት የእሸት ዛላዎች በቅለው አየ። ሰባቱም የቀጨጩ የእሸት ዛላዎች፥ ሰባቱን የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጡአቸው፤ ንጉሡም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ሕልም ማየቱን ተገነዘበ። ጠዋት ከመኝታው ሲነሣ መንፈሱ ታወከ፤ ስለዚህ በግብጽ ምድር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች ሁሉ አስጠርቶ ሕልሙን ነገራቸው፤ ነገር ግን የሕልሞቹን ትርጒም ለመግለጥ የቻለ አንድ እንኳ አልነበረም። በዚህ ጊዜ የወይን ጠጅ አሳላፊው ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁትን በደል ዛሬ አስታውሳለሁ፤ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ በእኔና በእንጀራ ቤት ኀላፊው ላይ ተቈጥተህ በዘበኞች አለቃ ቤት እንድንታሰር አድርገህ ነበር፤ በዚያ ሳለን በአንድ ሌሊት ሁለታችንም የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የተለያየ ትርጕም ነበረው። የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የነበረ አንድ ወጣት ዕብራዊ ከእኛ ጋር በእስር ቤት ነበር፤ የእያንዳንዳችንን ሕልም ለእርሱ ነገርነውና ተረጐመልን። ሁሉም ነገር እርሱ እንዳለው ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ማዕርጌ እንድመለስ ተደረገ የእንጀራ ቤቱ ኀላፊ ግን እንዲሰቀል ተደረገ።” ስለዚህ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት አዘዘ፤ ወዲያውኑ ከእስር ቤት ይዘውት መጡ፤ ጠጒሩን ተላጭቶ ልብሱን ከለወጠ በኋላ ወደ ንጉሡ ፊት ቀረበ። ንጉሡም ዮሴፍን “ሕልም አይቼ ነበር፤ ነገር ግን ማንም ሊተረጒመው አልቻለም፤ አንተ ሕልም የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰምቼአለሁ” አለው። ዮሴፍም “ንጉሥ ሆይ፥ እኔ ሕልም የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ትክክለኛውን ትርጒም ሊሰጥህ የሚችል እግዚአብሔር ነው” አለ። ንጉሡም እንዲህ አለ፤ “በሕልሜ በዓባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር፤ ሰባት የወፈሩና የሰቡ ላሞች ከወንዙ ወጥተው ሣር ሲበሉ አየሁ፤ ቀጥሎም አጥንቶቻቸው እስከሚታይ ድረስ የከሱ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ፤ እንደ እነርሱ የሚያስከፉ ላሞች በግብጽ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም። የከሱትና አስከፊ የሆኑት ላሞች በመጀመሪያ የወጡትን ሰባት የወፈሩ ላሞች ዋጡአቸው። ከዋጡአቸውም በኋላ እንደ ቀድሞው የከሱ ስለ ነበሩ፥ እንደ ዋጡአቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ በዚህ ጊዜ እኔ ከእንቅልፌ ነቃሁ። ደግሞም በሕልሜ በአንድ የእህል አገዳ ላይ ሰባት የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች አየሁ፤ ቀጥሎም የቀጨጩና በበረሓ ነፋስ ተመተው የሰለቱ ሰባት የእሸት ዛላዎች ታዩ። የቀጨጩትም ዛላዎች የሚያምሩትን ዛላዎች ዋጡአቸው፤ ያየኋቸውንም ሕልሞች ለአስማተኞች ነገርኩ፤ ነገር ግን ሕልሞቹን ማንም ሊተረጒምልኝ አልቻለም።” ዮሴፍም ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሁለቱም ሕልሞችህ ትርጒም አንድ ነው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር አስቀድሞ ገልጦልሃል፤ ሰባቱ የሚያምሩ ላሞች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ ሰባቱም ያማሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ የሁለቱም ትርጒም አንድ ነው። ከእነርሱም በኋላ የወጡት ሰባት የከሱትና አስከፊዎቹ ላሞች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ እንዲሁም ሰባቱ የቀጨጩና በበረሓ ነፋስ ተመተው የሰለቱ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ የሁለቱም ትርጒም አንድ ነው፤ ይኸውም ሰባት የራብ ዓመቶች ናቸው። ልክ እንደ ነገርኩህ ነው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር አስቀድሞ ገልጦልሃል፤ በመላው የግብጽ ምድር ላይ ታላቅ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመቶች ይመጣሉ። ከዚያ በኋላ ሰባት የራብ ዓመቶች ይመጣሉ፤ ራብ አገሪቱን በብርቱ ስለሚጐዳት እነዚያ የጥጋብ ዓመቶች ይረሳሉ። ተከታዩ የራብ ዘመን እጅግ አሠቃቂ ስለሚሆን የጥጋብ ጊዜ ፈጽሞ እንዳልነበረ ይሆናል። ሕልሙን ደጋግመህ ማየትህ የሚያመለክተው፥ ነገሩ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነና በቅርብ ጊዜም ውስጥ የሚፈጸም መሆኑን ነው። “እንግዲህ ጥበብና ማስተዋል ያለውን ሰው መርጠህ በአገሪቱ አስተዳዳሪ አድርገህ ሹመው፤ በሰባቱ የጥጋብ ዓመቶች አንድ አምስተኛውን ሰብል የሚሰበስቡ ሰዎችን መርጠህ ሹም። እነርሱ በሚመጡት የጥጋብ ዓመቶች ትርፍ የሆነውን ሰብል ሁሉ እንዲሰበስቡ እዘዛቸው፤ በየከተማውም እህል በጐተራ እንዲያከማቹና እንዲጠብቁት ሥልጣን ስጣቸው። ይህም የሚከማቸው እህል በግብጽ ምድር ላይ ወደፊት በሚመጡት ሰባት የራብ ዓመቶች ለአገሪቱ መጠባበቂያ ይሆናል፤ በዚህ ሁኔታ አገሪቱ በራብ ከመጐዳት ትድናለች።” ዕቅዱም ለፈርዖንና ለባለሟሎቹ ሁሉ መልካም ሆኖ ታያቸው፤ ንጉሡም “የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረበት ከዮሴፍ የተሻለ ሰው ከቶ አናገኝም” አላቸው። ስለዚህ ንጉሡ ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ይህን ሁሉ የገለጠልህ እግዚአብሔር ነው፤ ከማንኛውም ሰው ይልቅ አስተዋይና ብልኅ መሆንህ የተረጋገጠ ነው፤ ስለዚህ አንተን በአገሬ ላይ አስተዳዳሪ አድርጌ እሾምሃለሁ፤ ሕዝቡም ሁሉ ይታዘዝሃል፤ በሥልጣንም ከእኔ በቀር የሚበልጥህ የለም። እነሆ! አሁን በመላው የግብጽ ምድር ላይ አስተዳዳሪ አድርጌሃለሁ።” ንጉሡ የሥልጣኑ ምልክት ያለበትን የማኅተም ቀለበት ከጣቱ አውልቆ በዮሴፍ ጣት ላይ አደረገው፤ ከጥሩ ሐር የተሠራ ልብስ አለበሰው፤ በአንገቱም የወርቅ ሐብል አደረገለት። በንጉሡ ሁለተኛ ሠረገላ ላይ እንዲቀመጥ አደረገው፤ የንጉሡም የክብር ዘብ ከፊት ፊት እየሄደ “እጅ ንሡ! እጅ ንሡ!” ይል ነበር፤ ዮሴፍ በግብጽ ምድር ላይ አስተዳዳሪ ሆኖ የተሾመው በዚህ ዐይነት ነበር። ንጉሡም “እኔ ንጉሥ ብሆንም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ያለ አንተ ፈቃድ ማንም ሰው እጁን ወይም እግሩን ማንቀሳቀስ አይችልም” አለው። ፈርዖን ለዮሴፍ “ጻፍናት ፐዕናሕ” የሚል መጠሪያ ስም አወጣለት፤ አስናት ተብላ የምትጠራውን የጶጢፌራን ልጅ በሚስትነት ሰጠው፤ ጶጢፌራ ኦን ተብሎ በሚጠራው ከተማ ካህን ነበር። ዮሴፍ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንን ማገልገል ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር፤ ዮሴፍ ከቤተ መንግሥት ወጥቶ በመላው የግብጽ ምድር በመዘዋወር ጒብኝት ያደርግ ነበር፤ በሰባቱ የጥጋብ ዓመቶች ምድሪቱ እጅግ ብዙ ሰብል ሰጠች። በግብጽ አገር በእነዚያ ሰባት የጥጋብ ዓመቶች የተገኘውን ሰብል ሰብስቦ በየከተሞች አከማቸ፤ በየእያንዳንዱ ከተማ ያከማቸው እህል በዙሪያው ከሚገኙት እርሻዎች የተመረተ ነበር። በዚህ ዐይነት ዮሴፍ ብዛቱ እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የሆነ እጅግ ብዙ እህል አከማቸ፤ እህሉ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሣ እየሰፈረ መጠኑን ለማወቅ የነበረውን ዕቅድ ተወ። ሰባቱ የራብ ዓመቶች ከመጀመራቸው በፊት፥ ዮሴፍ ከጶጢፌራ ልጅ ከአስናት ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ጶጢፌራ ኦን ተብሎ በሚጠራው ከተማ ካህን ነበረ። ዮሴፍ “እግዚአብሔር የደረሰብኝን መከራና ዘመዶቼን እንድረሳ አደረገኝ” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ምናሴ ብሎ ጠራው፤ እንዲሁም “መከራ በተቀበልኩበት ምድር እግዚአብሔር ልጆች ሰጠኝ” በማለት ሁለተኛውን ልጅ ኤፍሬም ብሎ ጠራው። በግብጽ ምድር ጥጋብ የበዛባቸው ሰባቱ ዓመቶች ተፈጸሙ፤ ዮሴፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረው፥ ሰባቱ የራብ ዓመቶች መግባት ጀመሩ፤ በሌሎች አገሮች ሁሉ ራብ ሆነ፤ ይሁን እንጂ በመላው የግብጽ ምድር በቂ ምግብ ነበር። ራብ በመላው ግብጽ ምድር እየተስፋፋ በሄደ ጊዜ፥ ሕዝቡ ወደ ፈርዖን ሄዶ “ምግብ ስጠን!” ብሎ ጮኸ። ፈርዖንም “ወደ ዮሴፍ ሂዱና እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” ብሎ አዘዛቸው። ራቡ በመላው ግብጽ እየተስፋፋና እየበረታ ስለ ሄደ፥ ዮሴፍ ጐተራዎቹ ሁሉ ተከፍተው እህሉ ለግብጻውያን እንዲሸጥላቸው አደረገ። በዓለም ላይ ራብ ጸንቶ ስለ ነበር የልዩ ልዩ አገር ሕዝቦች ከዮሴፍ እህል ለመግዛት ወደ ግብጽ አገር መጡ።
ኦሪት ዘፍጥረት 41 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 41:1-57
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች