የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 4:1-15

ኦሪት ዘፍጥረት 4:1-15 አማ05

አዳም ከሚስቱ ከሔዋን ጋር ግንኙነት አደረገ፤ እርስዋም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ “በእግዚአብሔር ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” ስትል “ቃየል” የሚል ስም አወጣችለት። ቀጥሎም የቃየልን ወንድም አቤልን ወለደች፤ አቤል የበጎች ጠባቂ ሆነ፤ ቃየል ግን ገበሬ ሆነ። ከብዙ ቀን በኋላም ቃየል ካመረተው ሰብል ወስዶ ለእግዚአብሔር መባ አቀረበ። አቤልም ከበጎቹ መንጋ በመጀመሪያ የተወለደውን አንድ ጠቦት አመጣ፤ ካረደውም በኋላ የሰባውንና መልካም የሆነውን ብልት ሁሉ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እግዚአብሔርም በአቤልና በመሥዋዕቱ ደስ አለው። ለቃየልና ለመሥዋዕቱ ግን ግምት አልሰጣቸውም፤ በዚህ ምክንያት ቃየል በጣም ተቈጣ፤ ፊቱም በቊጣ ተኮሳተረ፤ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ቃየልን እንዲህ አለው፤ “የተቈጣኸውና ፊትህም በቊጣ የተኰሳተረው ለምንድን ነው? መልካም ነገር አድርገህ ቢሆን ኖሮ ተቀባይነት አይኖርህም ነበርን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በበርህ ላይ ያደባል፤ በቊጥጥሩ ሥር ሊያደርግህም ይፈልጋል፤ ሆኖም አንተ ልታሸንፈው ይገባል።” ከዚህ በኋላ ቃየል ወንድሙን አቤልን “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው፤ ወደ ሜዳም በሄዱ ጊዜ ቃየል በጠላትነት ተነሥቶ ወንድሙን አቤልን ገደለው። እግዚአብሔርም ቃየልን “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” ሲል ጠየቀው፤ ቃየልም “የት እንዳለ አላውቅም፤ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም ቃየልን እንዲህ አለው፤ “ምን አደረግህ? የፈሰሰው የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ እየጮኸ ነው፤ የወንድምህን ደም ከአንተ ለመቀበል አፍዋን በከፈተችው ምድር ላይ የተረገምክ ነህ። ምድርንም በምታርስበት ጊዜ ምንም ፍሬ አትሰጥህም፤ በምድር ላይም ስደተኛ ሆነህ ትንከራተታለህ።” ቃየልም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ይህ ቅጣት እኔ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው፤ እነሆ፥ ዛሬ ከምድር አባረርከኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ስደተኛና ተንከራታች እሆናለሁ፤ እንግዲህ ማንም ሰው ቢያገኘኝ ይገድለኛል።” እግዚአብሔር ግን “ማንም አይነካህም፤ አንተን የሚገድል ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል” አለው። ስለዚህ እግዚአብሔር ቃየልን ማንም ቢያገኘው እንዳይገድለው የሚያስጠነቅቅ ልዩ ምልክት አደረገለት።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}