የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 4:1-15

ዘፍጥረት 4:1-15 NASV

አዳም ሚስቱን ሔዋንን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ቃየንን ወለደች፤ “በእግዚአብሔር ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤል የበግ እረኛ፣ ቃየንም ዐራሽ ነበር። በአንድ ወቅት፣ ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረበ። አቤልም መጀመሪያ ከተወለዱት በጎቹ መካከል ስባቸውን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ በቃየንና በመሥዋዕቱ ግን አልተደሰተም፤ ስለዚህ ቃየን ክፉኛ ተናደደ፤ ፊቱም ጠቈረ። እግዚአብሔርም ቃየንን እንዲህ አለው፤ “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቈረ? መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኝምን? መልካም ባታደርግ ግን፣ ኀጢአት በደጅህ እያደባች ናት፤ ልታሸንፍህ ትፈልጋለች፤ አንተ ግን ተቈጣጠራት።” ቃየንም ወንድሙን አቤልን፣ “እስኪ ና፤ ወደ መስኩ እንውጣ” አለው፤ በመስኩም ሳሉ፣ ቃየን ወንድሙን አቤልን አጠቃው፤ ገደለውም። ከዚያም፣ እግዚአብሔር ቃየንን፣ “ወንድምህ አቤል የት ነው?” አለው። ቃየንም፣ “አላውቅም፤ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “ምንድን ነው ያደረግኸው? የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። እንግዲህ የተረገምህ ነህ፤ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን ከከፈተችው መሬት ትሰደዳለህ። ብታርሳትም ፍሬዋን አትለግስህም፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች ትሆናለህ።” ቃየንም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ቅጣቴ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው። እነሆ፤ ዛሬ ከምድሪቱ አባረርኸኝ፤ ከፊትህም እሸሸጋለሁ፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” እግዚአብሔር ግን፣ “የለም! እንደርሱ አይሆንም፤ ማንም ቃየንን ቢገድል፣ ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል” አለው፤ ስለዚህ፣ ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው እግዚአብሔር በቃየን ላይ ምልክት አደረገለት።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}