ያዕቆብ ተቀማጭነቱን አባቱ በኖረበት በከነዓን ምድር አደረገ። የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረበት ጊዜ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዚልፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር፤ ወንድሞቹ የሚፈጽሙትንም በደል እያመጣ ለአባቱ ይነግር ነበር። በስተርጅና የወለደው ስለ ሆነ ያዕቆብ ዮሴፍን ከሌሎች ልጆች ሁሉ አብልጦ ይወደው ነበር፤ ስለዚህም ጌጠኛ የሆነ እጀ ጠባብ ሰፋለት። ወንድሞቹም አባታቸው ከእነርሱ ይልቅ ዮሴፍን እንደሚወድ ባዩ ጊዜ በመቅናት ጠሉት፤ መልካም ቃልም ሊናገሩት አልወደዱም። አንድ ሌሊት ዮሴፍ ሕልም አየ፤ ሕልሙን ለወንድሞቹ በነገራቸውም ጊዜ ከቀድሞው ይበልጥ ጠሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ፤ እኛ ሁላችን በእርሻ ውስጥ የስንዴ ነዶ እናስር ነበር፤ የእኔ ነዶ ተነሣና ቀጥ ብሎ ቆመ፤ የእናንተ ነዶዎች ዙሪያውን ተሰብስበው ለእኔ ነዶ ሰገዱለት።” ወንድሞቹም “ታዲያ በእኛ ላይ ንጉሥ ሆነህ ልትገዛን ታስባለህን?” ብለው ጠየቁት። ስላየው ሕልምና ስለ ተናገረው ቃል ከበፊቱ ይበልጥ ጠሉት። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ሌላ ሕልም አይቶ ወንድሞቹን “እነሆ፥ ሌላ ሕልም አየሁ፤ በሕልሜም ፀሐይ፥ ጨረቃና ዐሥራ አንድ ከዋክብት ሰገዱልኝ” አላቸው። ይህንኑ ለወንድሞቹ የነገራቸውን ሕልም ለአባቱም በነገረው ጊዜ፥ አባቱ “ይህ ምን ዐይነት ሕልም ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም የምንሰግድልህ ይመስልሃልን?” በማለት ገሠጸው። የዮሴፍ ወንድሞች እጅግ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ይህን ነገር በልቡ እያሰላሰለ ይጠብቀው ነበር።
ኦሪት ዘፍጥረት 37 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 37:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos