ኦሪት ዘፍጥረት 29:15-30

ኦሪት ዘፍጥረት 29:15-30 አማ05

ላባ ያዕቆብን “ዘመዴ በመሆንህ ብቻ በነጻ ልታገለግለኝ አይገባህም፤ ስለዚህ ምን ያኽል ደመወዝ ላስብልህ?” አለው። ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ታላቂቱ ልያ፤ ታናሽቱ ራሔል ይባሉ ነበር። ልያ ዐይነ ልም ስትሆን፥ ራሔል ግን ቁመናዋ የሚያምር የደስ ደስ ያላት ነበረች። ያዕቆብ ራሔልን እጅግ ስለ ወደዳት “ራሔልን ብትድርልኝ ሰባት ዓመት አገለግልሃለሁ” አለ። ላባም “ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጥህ ይሻለኛል፤ እሺ ተስማምቼአለሁ፤ እዚሁ ከእኔ ጋር ኑር” አለው። ያዕቆብ ራሔልን ለማግባት ሰባት ዓመት አገለገለ፤ ይሁን እንጂ ራሔልን በጣም ይወዳት ስለ ነበር የቈየበት ጊዜ ጥቂት ቀን ብቻ መስሎ ታየው። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ላባን “እነሆ፥ የአገልግሎት ዘመኔ ተፈጽሞአል፤ ሚስት እንድትሆነኝ ልጅህን ስጠኝ” አለው። ላባም የሠርግ ድግስ አዘጋጅቶ በአቅራቢያው የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ ጠራ። ነገር ግን በመሸ ጊዜ ላባ በራሔል ምትክ ልያን ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም ወደ ልያ ገባ። ላባ ሴት አገልጋዩን ዚልፋን አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለልያ ሰጣት። በማግስቱ ጠዋት ያዕቆብ አብራው ያደረችው ልያ መሆንዋን ባወቀ ጊዜ ወደ ላባ ሄዶ “ይህ ያደረግህብኝ ነገር ምንድን ነው? ያገለገልኩህ ራሔልን ለማግኘት አልነበረምን? ታዲያ ለምን አታለልከኝ?” አለው። ላባም “ታላቂቱ ሳትዳር፥ ታናሺቱን መዳር የአገራችን ልማድ አይደለም፤ የልያ ሠርግ ሰባት ቀን እስኪሞላው ድረስ ጠብቅ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰባት ዓመት የምታገለግለኝ ከሆነ ራሔልን እሰጥሃለሁ” አለው። ያዕቆብም በነገሩ ተስማማ፤ ከልያ ጋር ሰባት ቀን ተሞሽሮ ከቈየ በኋላ፥ ላባ ልጁን ራሔልን ለያዕቆብ ዳረለት። ላባ ሴት አገልጋዩን ባላን አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለራሔል ሰጣት። ያዕቆብ ወደ ራሔልም ገባ፤ ከልያም አብልጦ ወደዳት፤ ከዚያ በኋላ ላባን ሰባት ዓመት አገለገለው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}