ይስሐቅ ያዕቆብን ጠርቶ መረቀው፤ እንዲህም ሲል አዘዘው፤ “ከነዓናዊት ሴት እንዳታገባ፤ ይልቅስ ተነሥተህ በመስጴጦምያ ወዳለው ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሂድ፤ እዚያም ከአጐትህ ከላባ ሴቶች ልጆች አንዷን አግባ፤ ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር ይባርክህ! ብዙ ልጆችም ይስጥህ! የብዙ ሕዝቦችም አባት ያድርግህ! አብርሃምን እንደ ባረከ አንተንና ዘርህን ይባርክ! ይህንንም ለአብርሃም ሰጥቶት የነበረውንና አንተም ስደተኛ ሆነህ የኖርክበትን ምድር ርስት አድርጎ ይስጥህ!” በዚህ ሁኔታ ይስሐቅ ያዕቆብን አሰናበተው፤ ያዕቆብም በመስጴጦምያ ወደሚኖረው ወደ ላባ ሄደ፤ ላባ የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም ነበረ፤ አባቱም ሶርያዊው ባቱኤል ነበር። ይስሐቅ ያዕቆብን እንደ መረቀውና ሚስት እንዲፈልግ ወደ መስጴጦምያ እንደ ላከው ዔሳው ተረዳ፤ ይስሐቅ ያዕቆብን ሲመርቀው፦ “ከነዓናዊት ሴት እንዳታገባ” ብሎ ያዘዘው መሆኑንም ሰማ፤ ያዕቆብ ለአባቱና ለእናቱ በመታዘዝ ወደ መስጴጦምያ መሄዱንም ተረዳ፤ በዚህም አባቱ ይስሐቅ የከነዓናውያንን ሴቶች እንደማይወድ ዔሳው ተገነዘበ፤ ስለዚህ ከዚህ በፊት ካገባቸው ሌላ በተጨማሪ ወደ አብርሃም ልጅ ወደ እስማኤል ሄዶ ልጁን ማሕላትን አገባ፤ እርስዋም የነባዮት እኅት ናት። ያዕቆብ ቤርሳቤህን ትቶ ወደ ካራን ለመሄድ ተነሣ፤ ፀሐይ በጠለቀች ጊዜ ወደ አንድ ስፍራ መጥቶ ዐረፈ፤ በዚያም አንድ ድንጋይ ተንተርሶ ተኛ፤ በሕልሙም ከመሬት እስከ ሰማይ የሚደርስ መሰላል አየ፤ በመሰላሉም የእግዚአብሔር መላእክት ወደ ላይ ይወጡና ወደ ታች ይወርዱ ነበር። እግዚአብሔርም በአጠገቡ ቆሞ እንዲህ አለው፤ “እኔ የአባትህ የአብርሃምና የይስሐቅ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ ለአንተና ለትውልድህ እንዲሆን ይህን የተኛህበትን ምድር እሰጥሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለሁ፤ እነርሱ በሁሉ አቅጣጫ ይዞታቸውን ያስፋፋሉ፤ በአንተና በዘርህ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ይባረካሉ። አይዞህ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በምትሄድበትም ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚህም ምድር በደኅና እመልስሃለሁ፤ የገባሁልህን ቃል ኪዳን ሁሉ እፈጽምልሃለሁ፤ ከቶም አልተውህም።” ያዕቆብም ከእንቅልፉ ነቃና “በእርግጥ እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅሁም ነበር” አለ። በጣም ፈርቶም ስለ ነበር “ይህ እንዴት የሚያስፈራ ቦታ ነው! ይህ የእግዚአብሔር ቤት መሆን አለበት፤ ወደ ሰማይ የሚያስገባው በር ይህ ነው” አለ። ያዕቆብ በማግሥቱ ጠዋት በማለዳ ተነሣ፤ ተንተርሶት የነበረውንም ድንጋይ መታሰቢያ እንዲሆን እንደ ሐውልት አቆመው፤ በላዩ ላይም የወይራ ዘይት አፈሰሰበት። ያንንም ስፍራ “ቤትኤል” ብሎ ሰየመው፤ ይህ ስፍራ ከዚያ በፊት ሎዛ እየተባለ ይጠራ ነበር። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ ለእግዚአብሔር ተሳለ፦ “ከእኔ ጋር ሆነህ በምሄድበት መንገድ ብትጠብቀኝ፥ የሚያስፈልገኝን ምግብና ልብስ ብትሰጠኝ፥ ወደ አባቴም ቤት በሰላም ብትመልሰኝ፥ አንተ አምላኬ ትሆናለህ፤ ይህ ለመታሰቢያነት ያቆምኩት ድንጋይ ወደ ፊት የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፤ ከምትሰጠኝም ሁሉ ከዐሥር አንዱን እጅ ለአንተ እሰጣለሁ።”
ኦሪት ዘፍጥረት 28 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 28:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos