ኦሪት ዘፍጥረት 2:15-23

ኦሪት ዘፍጥረት 2:15-23 አማ05

ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በዔደን የአትክልት ቦታ አኖረው፤ ይህንንም ያደረገው ሰው የአትክልቱን ቦታ እንዲያለማና እንዲንከባከበው ነው። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ “በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዛፎች ሁሉ ፍሬ ልትበላ ትችላለህ፤ ነገር ግን ከእርሱ በበላህበት ቀን በእርግጥ ስለምትሞት ደጉን ከክፉ ለመለየት የሚያስችል ዕውቀት ከሚሰጠው ዛፍ ፍሬ አትብላ።” ቀጥሎም እግዚአብሔር አምላክ “ሰው ብቻውን መኖሩ መልካም አይደለም፤ ስለዚህ ረዳት ጓደኛ እፈጥርለታለሁ” አለ። እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ እንስሶችንና ወፎችን ሁሉ ፈጠረ፤ ምን ዐይነት ስም እንደሚያወጣላቸው ለማየት ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳም ለእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር ያወጣለት ስም መጠሪያው ሆነ። በዚህ ዐይነት አዳም ለወፎቹና ለእንስሶቹ ሁሉ ስም አወጣላቸው፤ ለእርሱ ግን ረዳት ጓደኛ አልተገኘለትም ነበር። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከባድ እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገ፤ አንቀላፍቶም ሳለ ከጐኑ አጥንቶች አንዱን ወሰደና ባዶውን ቦታ በሥጋ ሞላው፤ እግዚአብሔር አምላክ ከአዳም ጐን የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም፥ “እነሆ በመጨረሻ እርስዋ ከአጥንቶቼ የተገኘች አጥንት ናት፤ ከሥጋዬም የተገኘች ሥጋ ናት፤ ከወንድ የተገኘች ስለ ሆነች ‘ሴት’ ትባል” አለ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}