የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 18

18
የሦስቱ እንግዶች ጒብኝት
1በመምሬ የወርካ ዛፎች አጠገብ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት፤ የተገለጠለትም በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ከዕለታት አንድ ቀን በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ነበር፤ 2ቀና ብሎም ሲመለከት ሦስት ሰዎች እዚያ ቆመው አየ፤ እንዳያቸውም ወዲያውኑ ሊያነጋግራቸው ወደ እነርሱ ሮጠ፤ ግንባሩም መሬት እስኪነካ ዝቅ ብሎ በመስገድ እጅ ነሣ፤ #ዕብ. 13፥2። 3እንዲህም አለ፤ “ጌታዬ ሆይ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ አልፈኸኝ እንዳትሄድ እለምንሃለሁ፤ 4እግራችሁን የምትታጠቡበት ውሃ እስካመጣላችሁ ድረስ በዚህ ዛፍ ጥላ ሥር ዐረፍ በሉ፤ 5ወደ እኔ ወደ አገልጋያችሁ በመምጣታችሁ ደስ ብሎኛል፤ ስለዚህ ለጒዞአችሁ ብርታት የሚሰጣችሁን ጥቂት ምግብ አምጥቼ እንዳስተናግዳችሁ ፍቀዱልኝ።”
እነርሱም “መልካም ነው፤ እንዳልከው አድርግ” አሉት።
6አብርሃም ወደ ድንኳኑ ሮጦ ሄደና ሣራን “ቶሎ ብለሽ ሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውሰጂና አቡክተሽ እንጀራ ጋግሪ” አላት። 7ከዚህ በኋላ አብርሃም ወደ መንጋው ሄደና ለግላጋውንና መልካሙን ጥጃ መርጦ ለአገልጋዩ ሰጠው፤ አገልጋዩም በፍጥነት ዐርዶ አወራርዶ አዘጋጀው፤ 8አብርሃም እርጎ፥ ወተትና ሥጋ ይዞ ሄደና ምግቡን ለእንግዶቹ አቀረበላቸው፤ እነርሱ ምግቡን በሚበሉበት ጊዜ አብርሃም ከዛፉ ሥር አጠገባቸው ቆሞ ያስተናግዳቸው ነበር።
ወንድ ልጅ እንደሚወለድለት ለአብርሃም የተሰጠው ተስፋ
9እነርሱም “ሚስትህ ሣራ የት አለች?” አሉት።
እርሱም “እዚያ ድንኳኑ ውስጥ ነች” አላቸው።
10ከሦስቱም እንግዶች አንዱ አብርሃምን “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው። #ሮም 9፥9።
እርሱም ይህን በሚናገርበት ጊዜ ሣራ በስተኋላው በድንኳኑ ደጃፍ ቆማ ታዳምጥ ነበር፤ 11አብርሃምና ሣራ በዕድሜአቸው መግፋት አርጅተው ነበር፤ የሣራም፥ ልጅ የመውለጃ ዕድሜዋ አልፎ ነበር። 12ስለዚህ ሣራ “እኔ አሁን እንዲህ ካረጀሁ በኋላ ጌታዬ አብርሃምም ካረጀ በኋላ እንዲህ ያለ ደስታ ሊኖረኝ ይችላልን?” ብላ በማሰብ ሳቀች። #1ጴጥ. 3፥6።
13እግዚአብሔርም አብርሃምን “ሣራ ‘እንደዚህ ካረጀሁ በኋላ ልጅ መውለድ እችላለሁን’ በማለት ስለምን ሳቀች? 14ከቶ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? እንደ ነገርኩህ የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው። #ሉቃ. 1፥37።
15ሣራ እጅግ ፈርታ ስለ ነበር “አልሳቅሁም” ብላ ካደች።
እርሱ ግን “በእርግጥ ስቀሻል” አላት።
አብርሃም ስለ ሰዶም ያቀረበው ምልጃ
16ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ለመሄድ ተነሡ፤ ሰዶምን ቊልቊል ወደሚያዩበት ስፍራም ደረሱ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ሄደ፤ 17እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፦ “እኔ የማደርገውን ነገር ከአብርሃም እሰውረዋለሁን? 18የአብርሃም ዘር ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ በእርሱም አማካይነት በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ይባረካሉ። 19ቅንና ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ እንዲጠብቁ ልጆቹንና ቤተሰቡን በመምከር ይመራቸው ዘንድ እኔ እርሱን መርጬዋለሁ፤ ልጆቹ ይህን ካደረጉ እኔም ለአብርሃም የሰጠሁትን ተስፋ ሁሉ እፈጽማለሁ።”
20ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “የሰዶምና የገሞራ ሕዝብ የሚፈጽሙት በደል ምን ያኽል እንደ ሆነ ሰምቼአለሁ፤ ኃጢአታቸውም እጅግ ከባድ መሆን አለበት፤ 21ስለ እነርሱ የሰማሁት ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ወደ እነርሱ እወርዳለሁ።”
22ከዚህ በኋላ ሁለቱ ሰዎች ወደ ሰዶም ለመሄድ ተነሡ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቆመ ቈየ፤ 23ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ በደል የሌለባቸውን ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር ታጠፋለህን? 24በከተማይቱ ውስጥ ኀምሳ ደጋግ ሰዎች ቢገኙ ከተማይቱን በሙሉ ትደመስሳለህን? ስለ ኀምሳው ደጋግ ሰዎች ስትል ከተማይቱ እንዳትጠፋ አታደርግምን? 25በደል ያልሠሩትን ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር ታጠፋለህ ብዬ አላስብም፤ ይህንን እንደማታደርገው አምናለሁ፤ ይህንንማ ካደረግህ ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር መቀጣታቸው ነው፤ ይህ ከቶ አይሆንም! የዓለም ሁሉ ፈራጅ በትክክል መፍረድ ይገባው የለምን?”
26እግዚአብሔርም “በሰዶም ከተማ ውስጥ በደል ያልሠሩ ኀምሳ ደጋግ ሰዎች ባገኝ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን ፈጽሞ አላጠፋም” አለ።
27አብርሃም እንደገና እንዲህ አለ፤ “እኔ ትቢያና ዐመድ የሆንኩ ከንቱ ሰው፥ ከጌታዬ ጋር በድፍረት በመነጋገሬ ይቅር በለኝ፤ 28ነገር ግን የደጋግ ሰዎች ቊጥር ኀምሳ መሆኑ ቀርቶ አርባ አምስት ቢሆን፥ አምስት ስለ ጐደለ ከተማይቱን በሙሉ ታጠፋለህን?”
እግዚአብሔርም “አርባ አምስት ደጋግ ሰዎች ባገኝ ከተማይቱን አላጠፋም” አለ።
29አብርሃምም “አርባ ብቻ እዚያ ቢገኙስ?” ብሎ እንደገና ጠየቀ።
እግዚአብሔርም “አርባ ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ።
30አብርሃምም “ጌታ ሆይ፥ እባክህ አትቈጣ፤ እንደገና ልናገር፤ ምናልባት ሠላሳ ብቻ ቢገኙስ?” አለ።
እግዚአብሔርም “ሠላሳ ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ።
31አብርሃምም “ጌታ ሆይ፥ አሁንም እንደገና በመናገሬ ይቅር በለኝ፤ ምናልባት ኻያ ቢገኙስ?” አለ፤
እግዚአብሔርም “ኻያ ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ።
32አብርሃምም “ጌታ ሆይ፥ እባክህ አትቈጣ አንድ ጊዜ ልናገር፤ ዐሥር ብቻ ቢገኙስ?” አለ።
እግዚአብሔርም “ዐሥር ቢገኙ ለእነርሱ ስል ከተማይቱን አላጠፋም” አለ። 33እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ተነጋግሮ ካበቃ በኋላ ከዚያ ስፍራ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ