የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 16:1-16

ኦሪት ዘፍጥረት 16:1-16 አማ05

የአብራም ሚስት ሣራይ ገና ልጅ አልወለደችለትም ነበር፤ ነገር ግን አጋር የምትባል አንዲት ግብጻዊት አገልጋይ ነበረቻት፤ ስለዚህ ሣራይ አብራምን “እነሆ፥ እግዚአብሔር ልጅ እንዳልወልድ ከልክሎኛል፤ ወደዚህች ወደ አገልጋዬ ግባ፤ ምናልባት በእርስዋ በኩል ልጅ አገኝ ይሆናል” አለችው። አብራምም ሣራይ ባለችው ነገር ተስማማ። ስለዚህ ሣራይ ግብጻዊት የሆነች አገልጋይዋን አጋርን ለአብራም ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው። ይህም የሆነው አብራም በከነዓን ዐሥር ዓመት ከኖረ በኋላ ነው። አብራም ወደ አጋር ገባ፤ ፀነሰችም፤ አጋር መፅነስዋን ባወቀች ጊዜ በእመቤትዋ ላይ ኮራች፤ ናቀቻትም። ሣራይም አብራምን “የደረሰብኝ በደል በአንተ ላይ ይሁን፤ እርስዋን ለአንተ የሰጠሁህ እኔ ራሴ ነኝ፤ እርስዋ ግን መፅነስዋን ካወቀችበት ጊዜ አንሥቶ እኔን መናቅ ጀምራለች፤ አሁንም ከእኔና ከአንተ ጥፋተኛው ማን እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይፍረድ!” አለችው። አብራምም “መልካም ነው፤ እርስዋ የአንቺ አገልጋይ ስለ ሆነች በቊጥጥርሽ ሥር ናት፤ የፈለግሺውን ነገር አድርጊ” አላት። ከዚህ በኋላ ሣራይ አጋርን እጅግ ስላሠቃየቻት አጋር ከቤት ወጥታ ኰበለለች። የእግዚአብሔር መልአክ አጋርን በበረሓ በሚገኘው በአንድ ምንጭ አጠገብ አገኛት፤ ይህም ምንጭ ወደ ሹር በሚወስደው መንገድ ላይ ነበር። መልአኩም “የሣራይ አገልጋይ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጂአለሽ?” አላት። እርስዋም “እኔ ከእመቤቴ ከሣራይ ሸሽቼ ነው” አለችው። መልአኩም “ወደ እመቤትሽ ተመለሽና አገልግያት” አላት። ደግሞም እንዲህ አላት፤ “ማንም ሊቈጥረው እስከማይችል ድረስ ዘርሽን አበዛዋለሁ፤ እነሆ፥ ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ እግዚአብሔር የሐዘን ለቅሶሽን ስለ ሰማልሽ ስሙን እስማኤል ትይዋለሽ። ነገር ግን እንደ ሜዳ አህያ ይሆናል፤ ሰውን ሁሉ ይቃወማል፤ ሰዎችም እርሱን ይቃወሙታል፤ ዘመዶቹን በመጥላት ተለይቶ ይኖራል።” አጋርም “በእርግጥ የሚያየኝን እግዚአብሔርን በዐይኔ አይቼ በሕይወት ኖርሁን?” በማለት ያነጋገራትን ጌታ “ኤልሮኢ” አለችው፤ ትርጒሙም “የሚያየኝ አምላክ” ማለት ነው። ስለዚህ ሰዎች በቃዴስና በባሬድ መካከል የሚገኘውን የውሃ ጒድጓድ “ብኤር ላሐይ ሮኢ” ብለው ይጠሩታል፤ ትርጒሙም “ሕያው የሆነውና የሚያየኝ አምላኬ ጒድጓድ” ማለት ነው። አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ እርስዋ የወለደችለትንም ልጅ “እስማኤል” ብሎ ስም አወጣለት፤ አብራም በዚያን ጊዜ 86 ዓመት ሆኖት ነበር።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}