የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 1:6-25

ኦሪት ዘፍጥረት 1:6-25 አማ05

ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ውሃውን ከውሃ የሚለይ ጠፈር ይሁን” አለ፤ በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር ጠፈርን ፈጠረ፤ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር “ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉት ውሆች ይለያዩ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔር ጠፈርን “ሰማይ” ብሎ ጠራው። ቀኑ መሸ፥ ሌሊቱም ነጋ፤ ሁለተኛ ቀን ሆነ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “የብሱ ግልጥ ሆኖ እንዲታይ ከሰማይ በታች ያለው ውሃ ሁሉ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። የብሱን “ምድር” ብሎ ጠራው፤ በአንድ ስፍራ የተሰበሰበውንም ውሃ “ባሕር” ብሎ ሰየመው፤ እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ምድር አትክልትን፥ የእህል አዝርዕትን፥ ፍሬ የሚያፈሩ የፍሬ ዛፎችንና ተክሎችን በየዐይነቱ ታብቅል” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። በዚህ ዐይነት ምድር አትክልትን፥ በየዐይነቱ የእህል አዝርዕትንና ዘር በውስጡ ያለውን ፍራፍሬ የሚያስገኙ ተክሎችን አበቀለች፤ እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ። ቀኑ መሸ፤ ሌሊቱም ነጋ፤ ሦስተኛ ቀን ሆነ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ቀንን ከሌሊት ለመለየት ልዩ ልዩ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ላይ ይሁኑ፤ ለዕለታት፥ ለክፍላተ ዓመትና ለዓመታት መለያ ምልክት ይሁኑ፤ ለምድር ብርሃን ለመስጠት በሰማይ ጠፈር ላይ ሆነው ያብሩ” እንዲሁም ሆነ። በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን ፈጠረ፤ ታላቁ ብርሃን በቀን፥ ታናሹ ብርሃን በሌሊት እንዲያበሩ አደረገ፤ እንዲሁም ከዋክብትን ፈጠረ፤ ለምድር ብርሃንን እንዲሰጡ እነዚህን ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ላይ አኖራቸው፤ ይህንንም ያደረገው በቀንና በሌሊት ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸውና ጨለማን ከብርሃን እንዲለዩ ነው። እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ። ቀኑ መሸ፤ ሌሊቱም ነጋ፤ አራተኛ ቀን ሆነ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ውሃ ሕይወት ባላቸው በልዩ ልዩ ፍጥረቶች የተሞላ ይሁን፤ ወፎችም ከምድር በላይ ባለው በሰማይ ጠፈር ይብረሩ” አለ። በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር ታላላቅ የባሕር አውሬዎችን፥ ሌሎችንም በውሃ ውስጥ የሚኖሩና የሚንቀሳቀሱ ልዩ ልዩ ፍጥረቶችን እንደየዐይነታቸው፥ እንዲሁም ልዩ ልዩ ወፎችን እንደየዐይነታቸው ፈጠረ። እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ። እግዚአብሔር “ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ የባሕርን ውሃ ይሙላ፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው። ቀኑ መሸ፤ ሌሊቱም ነጋ፤ አምስተኛ ቀን ሆነ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ምድር ሕይወት ያላቸው ፍጥረቶችን፥ እንደየዐይነታቸው እንስሶችን፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችንና አራዊትን እንደየዐይነታቸው ታስገኝ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር የምድር አራዊትን በየዐይነቱ፥ እንስሶችን በየዐይነታቸው በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችን በየዐይነታቸው ፈጠረ። እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}