የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ገላትያ ሰዎች 5:1-26

ወደ ገላትያ ሰዎች 5:1-26 አማ05

ክርስቶስ ነጻ ያወጣን በነጻነት እንድንኖር ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትጠመዱ። እነሆ! እኔ ጳውሎስ የምላችሁ ይህ ነው፤ “መገረዝ ያስፈልገናል” ብላችሁ ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም፤ “መገረዝ ያስፈልገኛል” ብሎ የሚገረዝ ሁሉ “ሕግን በሙሉ የመፈጸም ግዴታ አለበት” ብዬ እንደገና አስጠነቅቀዋለሁ። እናንተ ሕግን በመጠበቅ ለመጽደቅ የምትፈልጉ ሁሉ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፤ ከጸጋውም ርቃችኋል። እኛ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ የጽድቅን ተስፋ በእምነት እንጠባበቃለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚኖር በፍቅር ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም ጥቅም አይሰጠውም። ደኅና ትራመዱ ነበር፤ ታዲያ አሁን ለእውነት እንዳትታዘዙ የከለከላችሁ ማን ነው? እንዲህ ዐይነቱ ምክር ከጠራችሁ ከእግዚአብሔር የመጣ አይደለም። ይህም “ጥቂት እርሾ ሊጡን በሙሉ ያቦካዋል” እንደሚባለው ነው። ነገር ግን ከዚህ የተለየ ሌላ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ እርግጠኛ ሆኜ በጌታ እተማመናለሁ፤ ማንም ግራ የሚያጋባችሁ ቢኖር ቅጣቱን ይቀበላል። ወንድሞቼ ሆይ! እኔ እስከ አሁን የምሰብከው “ለመዳን መገረዝ ያስፈልጋል” እያልኩ ቢሆን ኖሮ እስከ አሁን ለምን ያሳድዱኝ ነበር? እንዲህ ቢሆን ኖሮ የክርስቶስ መስቀል ለሰዎች እንቅፋት መሆኑ ይቀር ነበር። እንግዲህ እነዚህ ግራ የሚያጋቡአችሁ ሰዎች ቢፈልጉ መገረዝ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ጃንደረባ ቢያደርጉ እወድ ነበር። ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል እንጂ ይህ ነጻነታችሁ የሥጋን ምኞት መፈጸሚያ ምክንያት አይሁን። ሕግ ሁሉ “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በአንድ ቃል ይፈጸማል። ነገር ግን እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። እንግዲህ በመንፈስ ተመርታችሁ ኑሩ፤ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙ እላለሁ። የሥጋ ምኞት ከመንፈስ ምኞት ጋር ይቃረናል፤ መንፈስና ሥጋ እርስ በእርሳቸው ይቃረናሉ፤ ስለዚህ እናንተ የምትፈልጉትን ማድረግ አትችሉም፤ በመንፈስ ብትመሩ ግን የሕግ ተገዢዎች አትሆኑም። የሥጋ ሥራዎች የታወቁ ናቸው፤ እነርሱም ዝሙት፥ ርኲሰት፥ ስድነት ጣዖትን ማምለክ፥ ሟርት፥ ጠላትነት፥ ንትርክ፥ ቅናት፥ ቊጣ፥ ራስ ወዳድነት፥ መለያየት፥ አድመኛነት፥ ምቀኝነት፥ ስካር፥ ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው፤ ከዚህ በፊት እንዳስጠነቀቅኋችሁ አሁንም ደግሜ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ እንደ እነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚያደርጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ደግነት፥ በጎነት፥ ታማኝነት፥ ገርነት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደእነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚቃረን ሕግ የለም፤ የኢየሱስ ክርስቶስ የሆኑት ሰዎች ሥጋን ከፍትወቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆንን በመንፈስ እንመራ። አንዱ ሌላውን ለክፉ በማነሣሣት እርስ በእርሳችን እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።