ወደ ገላትያ ሰዎች 3:1-9

ወደ ገላትያ ሰዎች 3:1-9 አማ05

እናንተ ሞኞች የገላትያ ሰዎች! ማን አፍዝ አደንግዝ አደረገባችሁ? ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ተሰቅሎ በፊት ለፊታችሁ በግልጥ ይታይ ነበር። ማወቅ የምፈልገው ይህን ብቻ ነው፤ ለመሆኑ እናንተ መንፈስ ቅዱስን የተቀበላችሁት ሕግን በመፈጸም ነውን? ወይስ የምሥራቹን ቃል ሰምታችሁ በማመን ነው? እናንተ በእግዚአብሔር መንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋዊ ጥረት መፈጸም ትፈልጋላችሁ፤ ለካ እስከዚህ ድረስ ሞኞች ናችሁ! በወንጌል ምክንያት የተቀበላችሁት መከራ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀረ ማለት ነውን? ይህን አድርጋችሁ ከሆነ በእርግጥ ከንቱ ሆኖ ቀርቶአል። እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጣችሁና በእናንተ ዘንድ ተአምራትን የሚያደርገው ሕግን በመፈጸማችሁ ነውን? ወይስ የምሥራቹን ቃል ሰምታችሁ በማመናችሁ ነው? ይህም “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እንግዲህ የሚያምኑ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ ዕወቁ። እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ ቅዱስ መጽሐፍ አስቀድሞ አይቶ “ሕዝቦች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” በማለት አስቀድሞ ለአብርሃም የምሥራቹን ቃል አብሥሮአል። ስለዚህ የሚያምኑ ሁሉ ከአመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።