የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 37:1-14

ትንቢተ ሕዝቅኤል 37:1-14 አማ05

የእግዚአብሔር ኀይል በእኔ ላይ መጣ፤ የእርሱም መንፈስ እኔን ወስዶ ብዙ አጥንቶች በተከማቸበት ሸለቆ ውስጥ አኖረኝ፤ በአጥንቶቹ መካከል አዙሮ አሳየኝ፤ በዚያም እጅግ የደረቁ በጣም ብዙ አጥንቶች ነበሩ። እርሱም “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ አጥንቶች ዳግመኛ ሕይወት የሚያገኙ ይመስልሃልን?” አለኝ። እኔም “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! ይህን የምታውቅ አንተ ብቻ ነህ” አልኩት። እርሱም እንዲህ አለ፦ “ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ብለህ ትንቢት ተናገር፦ እናንተ ደረቅ አጥንቶች የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላቸውን ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በውስጣችሁ እስትንፋስ በማስገባት እንደገና በሕይወት እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ። ጅማትና ሥጋ በመስጠት ቆዳ አለብሳችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አስገብቼ እንደገና በሕይወት እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ” እኔም በታዘዝኩት መሠረት ትንቢት ተናገርኩ፤ መናገርም እንደ ጀመርኩ የመንኰሻኰሽ ድምፅ ሰማሁ፤ አጥንቶቹም እርስ በርሳቸው እየተገጣጠሙ መያያዝ ጀመሩ። በመመልከት ላይ ሳለሁም አጥንቶቹ በጅማትና በሥጋ እንዲሁም በቈዳ ተሸፈኑ፤ እስትንፋስ ግን አልነበራቸውም። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ለነፋስ ትንቢት ተናገር፤ ነፋስ ከአራቱም ማእዘን መጥቶ ሕይወት እንዲያገኙ በእነዚህ በድኖች ላይ እንዲነፍስ ንገረው።” እኔም በታዘዝኩት መሠረት ትንቢት ተናገርሁ፤ በእነርሱ ሁሉ ውስጥ እስትንፋስ ገባባቸው፤ ሁሉም ሕይወት አግኝተው ቆሙ፤ እጅግ ብዙ ሠራዊትም ሆኑ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የእስራኤል ሕዝብ እኮ ልክ እንደእነዚህ አጥንቶች ናቸው፤ እነርሱ ‘እነሆ፥ አጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋ ቈርጠናል፤ የእኛ ጉዳይ አልቆለታል’ ይላሉ። ስለዚህም ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር መቃብራቸውን ከፍቼ እነርሱን በማውጣት ወደ እስራኤል ምድር የምመልሳቸው መሆኔን ንገራቸው። ሕዝቤ የተቀበሩበትን መቃብር ሁሉ ከፍቼ በማወጣቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ። እስትንፋሴን በእነርሱ ውስጥ አገባለሁ፤ በሕይወትም እንዲኖሩ አደርጋቸዋለሁ፤ በገዛ ምድራቸውም እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይህን የተናገርኩና የማደርገውም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”