የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 19

19
የሐዘን ሙሾ
1እግዚአብሔር ይህን የሐዘን ሙሾ ስለ እስራኤል መሳፍንት እንድደረድር ነገረኝ፦
2እናትህ በአንበሶች መካከል እንዴት ያለች እንስት አንበሳ ነበረች!
በደቦል አንበሶች መካከል ተዝናንታ
ግልገሎችዋን አሳደገች፤
3ከግልገሎችዋ አንዱን ተንከባክባ አሳደገችው
እርሱም ደቦል ሆነ፤ አደንንም ተማረ፤ ሰውንም መብላት ጀመረ።
4ሕዝቦች በእርሱ ላይ ጮኹበት
በቈፈሩት ጒድጓድም ውስጥ ተያዘ፤
በመንጠቆም አፍንጫውን ሰንገው
እየጐተቱ ወደ ግብጽ ወሰዱት።
5የነበራት ዓላማ እንዳልተሳካ አይታ ተስፋ በቈረጠች ጊዜ
ከግልገሎችዋ ሌላውን ወስዳ ተንከባክባ በማሳደግ ደቦል አንበሳ አደረገችው።
6ከሌሎች አንበሶች ጋር መዞር ጀመረ።
ደቦል አንበሳ ሆነ፤
ዐደንንም ተማረ፤ ሰውንም መብላት ጀመረ።
7ምሽጎቻቸውን ሰባበረ፤ ከተሞቻቸውንም አፈራረሰ፤
እርሱ ባገሣ ቊጥር
ምድሪቱና የሚኖሩባት ሰዎች ሁሉ ይሸበራሉ፤
8ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ ላይ ተነሡበት፤
ሁላቸውም ከየቦታው መጡ፤
መረባቸውን ዘረጉበት፤
በጒድጓዳቸውም ተያዘ፤
9በመንጠቆ ይዘው በወጥመድ ጎጆ ውስጥ አኖሩት፤
ወደ ባቢሎን ንጉሥ ዘንድም ወሰዱት፤
ድምፁ ዳግመኛ በእስራኤል ኰረብቶች እንዳይሰማ፥
ወደ እስር ቤት አስገቡት።
10እናትህ በውሃ አጠገብ እንደ ተተከለች የወይን ተክል ነበረች፤
እርስዋም ከውሃው መትረፍረፍ የተነሣ
በቅርንጫፎችዋና በፍሬ እንደ ተሞላች የወይን ተክል ሆነች፤
11ቅርንጫፎቹ ብርቱዎች ስለ ነበሩ፥
በትረ መንግሥት እስከሚገኝባቸው ድረስ አደጉ፤
የወይን ተክሉም ጥቅጥቅ ካለው ደን በላይ አደገ፤
ርዝመቱ ከብዙ ቅርንጫፎች ጋር ከፍ ብሎ ታየ።
12ነገር ግን በቊጣ ከስሩ ተነቅሎ ወደ ምድር ተጣለ።
ከበረሓ የሚነሣ የምሥራቅ ነፋስ አደረቀው፤
ፍሬዎቹም ረገፉ፤
ብርቱ የሆኑት ቅርንጫፎቹም ደረቁ፤
እሳትም በላቸው።
13አሁን ደግሞ በበረሓ፥
ውሃ በሌለበት ደረቅ ምድር ተተከለ።
14ከወይን ተክሉ ግንድ እሳት ወጣ፤
ቅርንጫፎቹንና ፍሬውን ሁሉ እሳት በላው፤
ቅርንጫፎቹ ዳግመኛ ብርቱ አይሆኑምና
በትረ መንግሥት መሆንም አይችሉም።
እንግዲህ በመደጋገም የሚደረደረው ሙሾ ይህ ነው።
እርሱም ለለቅሶ ያገለግላል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ