ትንቢተ ሕዝቅኤል 18
18
ሰው የሚቀጣው ራሱ በሠራው ኃጢአት ብቻ መሆኑ
1እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2“በእስራኤል ምድር ተደጋግሞ የሚነገር ይህ ምሳሌ ምንድን ነው? ‘ወላጆች ጐምዛዛ የወይን ፍሬ በሉ፤ ነገር ግን የልጆቻቸውን ጥርስ አጠረሰ’ ይላሉ፤
3“እኔ ሕያው እንደ መሆኔ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ዳግመኛ አትናገሩትም፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ። 4የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት የእኔ ነው፤ የወላጅም ሆነ የልጅ ሕይወት የእኔ መሆኑን ዕወቁ፤ ኃጢአት የሚሠራ ሰው ራሱ ይሞታል።
5“ሰው ጻድቅ፥ ፍትሓዊና ትክክለኛ ቢሆን፥ 6ለእስራኤላውያን ጣዖቶች አይሰግድም፤ ወይም በተከለከሉ መስገጃዎች የተሠዋውን ማንኛውንም ነገር አይመገብም፤ የሌላ ሰው ሚስትን አይደፍርም፤ ወይም የወር አበባ ከታያት ሴት ጋር ግንኙነት አያደርግም፤ 7ማንንም አይጨቊንም፤ ነገር ግን በመያዣ የያዘውን ይመልሳል፤ አይቀማም፤ ለተራበ ያበላል፤ ለታረዘ ያለብሳል፤ 8ገንዘቡን በአራጣ አያበድርም፤ ወይም ከፍተኛ ወለድ አይወስድም፤ ክፉ ነገር ከመሥራት ይቈጠባል፤ ጠበኞችን ለማስታረቅ ትክክለኛ ፍርድን ይሰጣል። 9እንዲህ ዐይነቱ ሰው ሕጌን ይፈጽማል፤ ሥርዓቴን ያከብራል፤ ያ ሰው ጻድቅ ስለ ሆነ በሕይወት ይኖራል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ። #ዘሌ. 18፥5።
10“ነገር ግን ይህ ሰው ዐመፀኛና ነፍሰ ገዳይ የሆነ፥ ከእነዚህም ጥፋቶች አንዱን የፈጸመ ልጅ ቢኖረው፥ 11አባቱ ከእነዚህ በደሎች አንዱን እንኳ የፈጸመ ባይሆን፥ ልጁ ግን በተራራ በጣዖት ቦታዎች የታረደውን ቢበላ፥ የሰውን ሚስት ቢደፍር፥ 12ድኾችንና ችግረኞችን ቢያስጨንቅ፥ ቢቀማ፥ ገንዘብ ሲያበድር በመያዣ ስም የወሰደውን ቢያስቀር፥ በአሕዛብ መስገጃ ስፍራዎች ጣዖትን ቢያመልክ አጸያፊ ነገሮችን ቢያደርግ፥ 13ገንዘቡን በአራጣ ቢያበድርና ከፍተኛ ወለድ ቢያስከፍል፥ ታዲያ እንዲህ ዐይነቱ ሰው በሕይወት ሊኖር ይችላልን? ከቶ በሕይወት ሊኖር አይችልም፤ ይህን ሁሉ አጸያፊ ነገር በማድረጉ በእርግጥ ይሞታል፤ ለሞቱም ተጠያቂው እርሱ ራሱ ይሆናል።
14“ነገር ግን ይህ ሰው በተራው ወንድ ልጅ ቢኖረው አባቱ የሚሠራውን ኃጢአት ሁሉ ቢያይ፥ ነገር ግን የአባቱን ምሳሌነት ባይከተል፥ 15ለእስራኤላውያን ጣዖቶች ባይሰግድ፥ ወይም በተከለከሉ መስገጃዎች የተሠዋውን ማንኛውንም ነገር ባይመገብ፥ የሌላ ሰው ሚስት ባይደፍር፥ 16ማንንም ባይጨቊን፥ ወይም የሰውን ሀብት ባይቀማ፥ ገንዘብ ሲያበድር በመያዣ የወሰደውን ባያስቀር፥ ለተራበ ቢያበላ፥ ለታረዘም ቢያለብስ፥ 17በድኾች ላይ ምንም ዐይነት ግፍ ባይሠራ፥ ገንዘቡን በአራጣ አበድሮ ከፍተኛ ወለድ ባያስከፍል፥ ሕጌን ቢያከብር፥ ሥርዓቴን ቢከተል፥ እንዲህ ዐይነቱ ሰው በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አባቱ በሠራው ኃጢአት ምክንያት አይሞትም። 18አባቱ ግን ብዝበዛን ስለ ፈጸመ፥ ወንድሙን ስለ ቀማና በሕዝቡ ዘንድ መልካም ያልሆነውን ነገር ስላደረገ በበደሉ ይሞታል።
19“ ‘ታዲያ ልጁ በአባቱ ኃጢአት ምክንያት ያልተቀጣው ስለምንድን ነው?’ ትሉ ይሆናል፤ ልጁ ትክክልና መልካም የሆነውን ነገር አድርጎአል፤ ሕጌን አክብሮአል፤ ስለዚህ እርሱ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ 20ሞት የሚገባው ኃጢአት ለሚሠራ ሰው ብቻ ነው፤ ልጅ ስለ አባቱ ኃጢአት አይቀጣም፤ አባትም ስለ ልጁ ኃጢአት አይቀጣም፤ ደግ ሰው በደግነቱ መልካም ዋጋውን ያገኛል፤ ክፉ ሰውም በክፋቱ ይቀጣል። #ዘዳ. 24፥16።
21“ክፉ ሰው ኃጢአት መሥራትን ትቶ ሕጌን ቢጠብቅ፥ ትክክልና መልካም የሆነውን ነገር ቢያደርግ፥ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም፤ 22ትክክል የሆነውን ነገር ስላደረገም የሠራው ኃጢአት ሁሉ ይቅር ተብሎለት በሕይወት ይኖራል። 23እኔ በክፉ ሰው ሞት የምደሰት ይመስላችኋልን? አይደለም፤ እኔ ደስ የሚለኝ ስለ ኃጢአቱ ንስሓ ገብቶ በሕይወት በሚኖር ሰው ነው፤ ይላል ልዑል እግዚአብሔር።
24“ነገር ግን ደግ ሰው መልካም ማድረጉን ትቶ ክፉ ሰዎች የሚያደርጉአቸውን ክፉና አጸያፊ ነገሮች ማድረግ ቢጀምር፥ በሕይወት መኖር የሚችል ይመስላችኋልን? አይደለም! እንዲያውም ያደረገው የደግነት ሥራ ሁሉ አይታሰብለትም፤ ባለመታመኑና ኃጢአተኛም በመሆኑ ምክንያት ይሞታል።
25“እናንተም ‘እንዲህ ከሆነ እግዚአብሔር የሚያደርገው ነገር ትክክል አይደለም’ ትሉ ይሆናል፤ እናንተ እስራኤላውያን እኔን አድምጡ፤ እኔ የማደርገው ነገር ሁሉ ትክክል እንዳልሆነ ታስባላችሁን? ነገር ግን ትክክል ያልሆነው የእናንተ አካሄድ ነው። 26ጻድቅ ሰው መልካም ማድረጉን ትቶ ክፉ ሥራ ሠርቶ ቢሞት የሚሞተው በኃጢአቱ ምክንያት ነው፤ 27እንዲሁም ክፉ ሰው ኃጢአት መሥራት ትቶ ፍትሓዊና ትክክለኛ ሥራ ቢሠራ ሕይወቱን ያድናል፤ 28የሚያደርገው ነገር ከንቱ መሆኑን ተገንዝቦ ኃጢአት መሥራቱን ስለ ተወ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም፤ 29እናንተ እስራኤላውያን ግን ‘ልዑል እግዚአብሔር የሚያደርገው ነገር ትክክል አይደለም’ ትላላችሁ፤ ታዲያ የእኔ ሥራ ትክክል ያልሆነ ይመስላችኋልን? ትክክል ያልሆነውስ የእናንተ አካሄድ ነው።
30“አሁንም እኔ ልዑል እግዚአብሔር ለእናንተ ለእስራኤላውያን የምላችሁ ይህ ነው፤ በክፉ ሥራችሁ እያንዳንዳችሁን እቀጣለሁ፤ ስለዚህ ከምታደርጉት ክፋት ተመለሱ፤ አለበለዚያ ኃጢአታችሁ ያጠፋችኋል። 31ከክፉ ሥራችሁ ሁሉ ተላቃችሁ አዲስ መንፈስና አዲስ ልብ ይኑራችሁ፤ እናንተ እስራኤላውያን ለምን ትሞታላችሁ? 32እኔ ማንም ሰው እንዲሞት አልፈልግም፤ ስለዚህ ሁላችሁም ከኃጢአታችሁ ተመልሳችሁ በሕይወት ኑሩ፤” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 18: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997