ትንቢተ ሕዝቅኤል 12
12
የነቢዩ ሕዝቅኤል መሰደድ
1እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! አንተ የምትኖረው ዐመፀኞች በሆኑ ሕዝብ መካከል ነው፤ እነርሱ ዐመፀኞች ከመሆናቸው የተነሣ ዐይን እያላቸው አያዩም፤ ጆሮም እያላቸው አይሰሙም። #ኢሳ. 6፥9-10፤ ኤር. 5፥21፤ ማር. 8፥18።
3“ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ! የስደት ዕቃህን ጠቅልለህ አዘጋጅ፤ እነርሱ እያዩም የስደት ጒዞህን በቀን ጀምር፤ እንደ ስደተኛ ከቦታህ ተነሥተህ ወደ ሌላ ቦታ ሂድ፤ ዐመፀኞች ቢሆኑም እንኳ ያስተውሉ ይሆናል። 4እንደ ስደተኛ እነርሱ እያዩህ የጒዞ ዕቃህን በቀን ታዘጋጃለህ፤ ስደተኞች እንደሚያደርጉትም እነርሱ እያዩህ ወደ ማታ ጊዜ ወጥተህ ሂድ። 5በሚመለከቱህም ጊዜ የቤትህን ግድግዳ ሸንቁረህ ቀዳዳ አብጅ፤ ዕቃህንም በዚያ ቀዳዳ አሾልከህ አውጣው፤ 6የምትሄድበትን ስፍራ እንዳታይ ዕቃህን በትከሻህ ተሸክመህ ፊትህን በመሸፈን በጨለማ ስትሄድ ይመልከቱህ፤ እኔም ለእስራኤላውያን ምልክት አድርጌሃለሁ።”
7እኔም እግዚአብሔር ያዘዘኝን ሁሉ አደረግሁ፤ በዚያኑ ቀን እንደ ስደተኛ ዕቃዬን ጠቀለልኩ፤ ቀኑም ሲመሽ ግድግዳውን በእጄ ነድዬ ቀዳዳ አበጀሁና በዚያ በኩል ዕቃዬን አወጣሁ፤ ሰዎቹም ሁሉ እያዩኝ የተጠቀለለውን ዕቃዬን በትከሻዬ ላይ አድርጌ በጨለማ ሄድኩ።
8በማግስቱም ጠዋት እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፤ 9“የሰው ልጅ ሆይ! እነዚያ ዐመፀኞች እስራኤላውያን ‘እነሆ ይህ የምታደርገው ነገር ሁሉ ምንድን ነው?’ ብለው አልጠየቁህምን? 10ስለዚህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለውን ንገራቸው፤ ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም ላይ ለሚያስተዳድረው መስፍንና እዚያም ለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ የተነገረ ነው። 11ይህም አንተ ያደረግኸው ነገር ሁሉ በእነርሱ ላይ ሊፈጸም ለተቃረበው ነገር ምልክት መሆኑን አስታውቃቸው፤ እነርሱም ስደተኞችና ምርኮኞች ይሆናሉ ማለት ነው። 12እነርሱን የሚያስተዳድረው መስፍን ዕቃውን ጠቅልሎ በትከሻው በመሸከም እነርሱ ግድግዳ ነድለው በሚያወጡለት ቀዳዳ ሾልኮ በጨለማ ይሰደዳል፤ ዐይኑንም ስለሚሸፍን ምድሪቱን አያይም። 13ነገር ግን እኔ መረቤን ዘርግቼ አጠምደዋለሁ፤ በዐይኑ ሳያያት ወደሚሞትባት ወደ ባቢሎን ከተማ አመጣዋለሁ፤ #2ነገ. 25፥7፤ ኤር. 52፥11። 14የቅርብ አማካሪዎቹንና የክብር ዘብ ጠባቂዎቹን ሁሉ በየአቅጣጫው እበትናቸዋለሁ፤ ከኋላቸውም ሆኜ በሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ።
15“በባዕዳን ሕዝቦችና አገሮች መካከል በምበትናቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ፤ 16ነገር ግን ከእነርሱ ጥቂቶቹን ከጦርነት፥ ከራብና ከቸነፈር እንዲተርፉ አደርጋለሁ፤ በዚህም ዐይነት በሕዝቦች መካከል ሲኖሩ ሥራቸው ምን ያኽል አጸያፊ እንደ ነበር ይገነዘባሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።”
በፍርሃት የሚሸበረው ነቢይ ምልክት
17እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 18“የሰው ልጅ ሆይ! በምትበላበት ጊዜ በፍርሃት ብላ፤ በምትጠጣበትም ጊዜ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ጠጣ፤ 19በምድሪቱ ለሚኖሩ ሕዝብ ጌታ እግዚአብሔር በእስራኤል ምድር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሕዝብ እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው፦ ‘በምድሪቱ በሚኖሩ ሰዎች ዐመፅ ምክንያት ምድሪቱ በጠቅላላ ስለምትራቈት ምግባቸውን የሚበሉት በፍርሃት ነው፤ ውሃቸውንም የሚጠጡት ተስፋ በመቊረጥ ነው። 20አሁን በሕዝብ ተሞልተው የሚታዩ ከተሞች ይጠፋሉ፤ አገሪቱም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ በዚያን ጊዜ እነርሱ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።’ ”
ተወዳጅ ምሳሌና የተጠላ የትንቢት ቃል
21እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 22“የሰው ልጅ ሆይ! ራእዩ ሁሉ ተግባራዊ ሳይሆን ቀኖቹ ተራዘሙ ተብሎ ስለ እስራኤል ምድር የሚነገረው ይህ ምሳሌ ምንድን ነው? 23እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለዚህ ጉዳይ የምለውን ንገራቸው፤ ይህ ምሳሌ እዚሁ ላይ እንዲያበቃ አደርገዋለሁ፤ ዳግመኛም በእስራኤል አይነገርም፤ በዚህ ፈንታ ‘እነሆ ጊዜው ደርሶአል፤ የትንቢቱም ቃል ሁሉ ሊፈጸም ነው!’ ብለህ ንገራቸው።
24“በእስራኤል ሕዝብ መካከል ሐሰተኛ ራእይ ወይም ሟርት ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አይነገርም። 25እኔ እግዚአብሔር በቀጥታ እናገራለሁ፤ የምናገረውም ቃል ሁሉ ይፈጸማል፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ አይዘገይም፤ እናንተ ዐመፀኞች ‘በእናንተ ላይ አመጣለሁ’ ብዬ በማስጠንቀቅ የተናገርኩትን ሁሉ በሕይወታችሁ ዘመን እንዲፈጸም አደርጋለሁ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።”
26እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 27“የሰው ልጅ ሆይ! እስራኤላውያን የአንተ ራእይና ትንቢት ‘ከብዙ ዘመን በኋላ የሚፈጸም ነው’ ብለው ይናገራሉ፤ 28ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር የምላቸውን ንገራቸው፤ እኔ የተናገርኩት ሁሉ ይፈጸማል፤ ከቶም አይዘገይም፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 12: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997