እግዚአብሔርም ሙሴን “በንጉሡ በፈርዖን ላይ የማደርገውን አሁን ታያለህ፤ በኀይሌ ተገዶ ሕዝቤን ይለቃል፤ በኀያል ክንዴም ተሸንፎ ያባርራቸዋል።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ሁሉን የምችል አምላክ (ኤልሻዳይ) መሆኔን በማስረዳት ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ተገልጬላቸዋለሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በተሰኘው ቅዱስ ስሜ አማካይነት ግን አልተገለጥኩላቸውም። እንደ ስደተኞች ሆነው የሚኖሩባትን የከነዓንን ምድር ላወርሳቸው ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ። እነሆ፥ አሁንም ግብጻውያን ባርያዎች አድርገው የሚያስጨንቁአቸውን የእስራኤላውያንን መራራ ጩኸት ሰምቼአለሁ፤ የገባሁትንም ቃል ኪዳን አስታውሼአለሁ። ስለዚህም ለእስራኤላውያን የምለውን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ግብጻውያን ከሚያደርሱባችሁ የባርነት ጭቈና በማዳን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ አሠቃቂ ቅጣት አመጣባቸው ዘንድ የኀይል ክንዴን በእነርሱ ላይ አነሣለሁ፤ እናንተንም እታደጋችኋለሁ፤ የእኔ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ፤ ከግብጽ ባርነትም ነጻ በማወጣችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ መሆኔን ታውቃላችሁ፤ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ አወርሳቸው ዘንድ በመሐላ ቃል ኪዳን ወደገባሁባት ምድር አመጣችኋለሁ፤ ርስትም አድርጌ አወርሳችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” ሙሴም ይህን ሁሉ ለእስራኤላውያን ነገረ፤ እነርሱ ግን በወደቀባቸው ጨካኝ ጭቈና ምክንያት መንፈሳቸው ተሰብሮ ስለ ነበረ ሊያዳምጡት አልፈለጉም። እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ግብጽ ንጉሥ ሄደህ እስራኤላውያንን ከአገርህ እንዲወጡ ልቀቃቸው ብለህ ንገረው።” ነገር ግን ሙሴ “ወገኖቼ እስራኤላውያን እንኳ አልሰሙኝም፤ ታዲያ፥ ንጉሡ እንዴት ሊሰማኝ ይችላል? እንደምታየኝ እኔ ኰልታፋ ነኝ” ሲል መለሰ።
ኦሪት ዘጸአት 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 6:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች