ኦሪት ዘጸአት 38
38
የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ አሠራር
(ዘፀ. 27፥1-8)
1የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ እርሱም አራት ማእዘን ሆኖ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ርዝመት፥ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ስፋት፥ አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ቁመት ነበረው፤ 2ከመሠዊያው ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ጒጦችንም በአራቱ ማእዘን አደረገበት ሁሉንም በነሐስ ለበጠው። 3በመሠዊያው ላይ ያሉትንም የመገልገያ ዕቃዎች፥ ድስቶችንም፥ የእሳት መጫሪያዎቹንም፥ ጐድጓዳ ሳሕኖችንም፥ ሜንጦዎቹንም፥ ማንደጃዎቹንም ከነሐስ ሠራ፤ 4መረብ የሚመስል የነሐስ መከላከያ ሠራ፤ እርሱንም እስከ መሠዊያ ግማሽ ቁመት እንዲደርስ አድርጎ በመሠዊያው ክፈፍ ሥር አኖረው፤ 5ለመሸከሚያ የሚያገለግሉ መሎጊያዎች መሹለኪያ ይሆኑ ዘንድ አራት ቀለበቶችን ሠርቶ በአራቱ ማእዘኖች ላይ አደረጋቸው። 6መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሠርቶ በነሐስ ለበጣቸው። 7በመሠዊያው ጐንና ጐን ባሉት ቀለበቶችም ውስጥ አስገባቸው፤ መሠዊያው ከሳንቃ የተሠራ ሆኖ ውስጡ ክፍት ነበር።
የመታጠቢያው ሳሕን አሠራር
(ዘፀ. 30፥18)
8የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫውን ጭምር ከነሐስ ሠራ፤ ነሐሱም የተገኘው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ የሚያገለግሉ ሴቶች ካመጡት የነሐስ መስተዋቶች ነው።
የድንኳኑ መግቢያ ክፍል አሠራር
(ዘፀ. 27፥9-19)
9ለተቀደሰው ድንኳን መግቢያ ክፍል መጋረጃዎችን ከጥሩ በፍታ ሠራ፤ የመጋረጃዎቹም ርዝመት በደቡብ በኩል አርባ አራት ሜትር ነበር፤ 10መጋረጃዎችን የሚደግፉ ኻያ ምሰሶዎችንና ኻያ እግሮቻቸውን ከነሐስ ሠራ፤ የምሰሶዎቹንም ኩላቦችና ዘንጎች ከብር ሠራ፤ 11ከሰሜንም በኩል የአደባባዩ አሠራር እንደዚሁ ነበር፤ 12በምዕራብ በኩል ኻያ ሁለት ሜትር ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ነበሩ፤ እነርሱም ዐሥር እግሮች ያሉአቸው ዐሥር ምሰሶዎች ነበሩአቸው፤ ምሰሶዎቹም ከብር የተሠሩ ኩላቦችና ዘንጎች ነበሩአቸው። 13የመግቢያው ደጅ ባለበት በምሥራቅ በኩል የአደባባዩ ስፋት ኻያ ሁለት ሜትር ነበር። 14በአንድ በኩል ያለው የበሩ መጋረጃ ስድስት ሜትር ከስድሳ ሳንቲ ሜትር ተኩል ርዝመት፥ ሦስት ምሰሶዎችና ሦስት እግሮችም ነበሩት። 15እንዲሁም በሌላው በኩል በአደባባዩ ደጅ በዚህና በዚያ ስድስት ሜትር ከስድሳ ሳንቲ ሜትር ርዝመት፥ ሦስት ምሰሶዎችና ሦስት እግሮች ነበሩት። 16በድንኳኑ መግቢያ ዙሪያ ያሉት መጋረጃዎች ሁሉ ከጥሩ በፍታ የተሠሩ ነበሩ፤ 17የምሰሶዎቹ እግሮች የተሠሩት ከነሐስ ነበር፤ ኩላቦቹ ዘንጎቹና የምሰሶዎቹ ጫፎች መሸፈኛዎች ከብር የተሠሩ ነበሩ፤ በአደባባዩ ዙሪያ ያሉት ምሰሶዎች ሁሉ በብር ዘንጎች የተያያዙ ነበሩ፤ 18ወደ ድንኳኑ የሚያስገባው ደጃፍ መጋረጃ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ በፍታ ተፈትሎ በእጅ ጥበብ ካጌጠ ቀጭን ሐር የተሠራ ነበር፤ እርሱም እንደ ድንኳኑ በር መግቢያ መጋረጃዎች ሁሉ ርዝመቱ ዘጠኝ ሜትር ቁመቱም ሁለት ሜትር ነበር፤ 19አራት የነሐስ እግሮች ባሉአቸው አራት ምሰሶዎች ተደግፎ ነበር፤ ኩላቦቻቸው፥ ጫፎቻቸውና ዘንጎቻቸው ከብር የተሠሩ ነበሩ፤ 20ለድንኳኑና በዙሪያው ላለው የአደባባይ አጥር መጋረጃዎች የሚያገለግሉት ካስማዎች ሁሉ የተሠሩት ከነሐስ ነበር።
በድንኳኑ ውስጥ በአገልግሎት ላይ የሚውሉ የብረታ ብረት ዐይነቶች
21በሙሴ ትእዛዝ፥ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር መሪነት የሌዋውያን ተግባር የሆነው የተቀደሰው ድንኳን ዕቃዎች ዝርዝር ቈጠራ እነዚህ ናቸው፦
22ከይሁዳ ነገድ የሑር የልጅ ልጅ የሆነው የኡሪ ልጅ ባጽልኤል፥ እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሁሉን ነገር ሠራ፤ 23ከእርሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነው የአሒሳማክ ልጅ አሆሊአብም አንጥረኛ፥ ፕላን አውጪ ባለሞያ፥ እንዲሁም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ እየጠለፈ ጥሩ በፍታ የሚሠራ ሸማኔ ነበር።
24ለተቀደሰው ድንኳን መሥሪያ ይሆን ዘንድ ለእግዚአብሔር ተለይቶ የተሰጠ ወርቅ በሙሉ በይፋ በታወቀው ሚዛን ልክ አንድ ሺህ ኪሎ ግራም ይመዝን ነበር 25ከመላው ከተቈጠረው ሕዝብ የተሰበሰበው ብር መጠን በይፋ በታወቀው ሚዛን ልክ ሦስት ሺህ አራት መቶ ሠላሳ ኪሎ ግራም ነበር፤ 26ይህም በሕዝብ ቈጠራ ጊዜ የተመዘገቡት ሰዎች እያንዳንዳቸው በይፋ በታወቀው ሚዛን ልክ የከፈሉትን ድርሻ ጠቅላላ ድምር የሚያኽል ነበር፤ በሕዝብ ቈጠራ የተመዘገቡትም ኻያ ዓመት የሞላቸውና ከዚያም በላይ የሆኑት ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ኀምሳ ወንዶች ነበሩ። 27ከብሩም ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ የሚሆነው ለተቀደሰው ድንኳንና ለመጋረጃዎች መቆሚያ የሚሆኑ አንድ መቶ እግሮች የተሠሩበት ነበር፤ ይኸውም ለእያንዳንዱ እግር ሠላሳ አራት ኪሎ ግራም ተመድቦለት ነው። 28በቀረውም ሠላሳ ኪሎ ብር ባጽልኤል ለምሰሶዎቹ ዘንጎችን፥ ኩላቦችንና ጒልላቶችን ሠራ። 29ለእግዚአብሔር ተለይቶ የተሰጠ ነሐስ ሁለት ሺህ አራት መቶ ኻያ አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ነበር፤ 30ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ የሆነው ደጃፍ የሚቆምባቸውን እግሮች፥ ከነሐስ መከላከያው ጋር የነሐስ መሠዊያውን፥ ለመሠዊያው መገልገያ የሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ ከዚህ ነሐስ ሠራ፤ 31በዙሪያ ያለው የአደባባይ አጥርና ወደ አደባባዩ የሚያስገባው ደጃፍ የሚቆሙባቸውን እግሮች፥ እንዲሁም የድንኳኑና በዙሪያው ያለውን የአደባባይ አጥር ካስማዎችን ሁሉ ሠራ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 38: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997