ኦሪት ዘጸአት 39
39
የካህናት ልብስ አሠራር
(ዘፀ. 28፥1-14)
1ካህናቱ በተቀደሰው ስፍራ ሲያገለግሉ የሚለብሱአቸውን እጅግ የተዋቡትን የካህናት ልብሶች ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ሠሩ፤ የአሮንንም የክህነት ልብሶች እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሠሩ።
2ኤፉዱንም ከወርቅ ክር፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና፥ ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠሩ፤ 3ወርቁንም ቀጥቅጠው ስስ በማድረግ እንደ ክር አድርገው ቈራረጡት፤ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለም ጥሩ በፍታ ጋር በጥበብ አሠራር ጠለፉት። 4ለኤፉዱም ማንገቻ በትከሻ ላይ የሚወርዱ ሁለት ጥብጣቦች ሠርተው ኤፉዱ እንዲጠብቅ በጐንና በጐኑ አያያዙአቸው። 5እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከወርቅ ክር፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና፥ ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ በብልኀት የተጠለፈው ቀበቶ አንድ ወጥ በመሆን ከኤፉዱ ጋር ተያይዞ ተሠራ። 6የመረግድ ድንጋዮችንም አዘጋጅተው በወርቅ ፈርጥ ላይ አስቀመጡአቸው፤ በእነርሱም ላይ የዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ስሞች እንደ ቀለበት ማኅተም ተቀርጸውባቸው ነበር፤ 7እነርሱም እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ዐሥራ ሁለቱን የእስራኤል ነገድ በመወከል እንዲታሰቡ በትከሻ ላይ በሚወርዱት በኤፉዱ ጥብጣቦች ላይ አኖሩአቸው።
የደረት ኪስ አሠራር
(ዘፀ. 28፥15-30)
8የደረቱንም ኪስ ኤፉዱ ከተሠራባቸው ተመሳሳይ ነገሮች በተመሳሳይ የጥበብ ጥልፍ ሠሩት፤ 9እርሱም በሁለት የታጠፈ አራት ማእዘን ሆኖ ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ 10የከበሩ ድንጋዮችንም በአራት ረድፍ አደረጉበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮንና የሚያብረቀርቅ ዕንቊ፤ 11በሁለተኛውም ረድፍ በሉር፥ ሰንፔርና ዐልማዝ፥ 12በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፥ ኬልቄዶንና አሜቴስጢኖስ፥ 13በአራተኛው ረድፍ ቢረሌ፥ መረግድና ኢያስጲድ፤ እነዚህ ሁሉ በወርቅ ፈርጥ ላይ የተቀመጡ ነበሩ። 14የከበሩት ድንጋዮች ዐሥራ ሁለቱን የእስራኤል ነገድ በመወከል እንዲታሰቡ በእያንዳንዱ ድንጋይ ላይ ከዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ስሞች አንዱ ስም ተቀርጾበታል። 15ለደረቱ ኪስም እንደ ገመድ የተጐነጐኑትን ድሪዎች ከጥሩ ወርቅ ሠሩ። 16ሁለት የወርቅ ፈርጦችና ሁለት የወርቅ ቀለበቶችም ሠርተው፥ ሁለቱን ቀለበቶች በደረት ኪሱ በላይ በኩል ካሉት ማእዘኖች ጋር አያያዙአቸው። 17ሁለቱንም የወርቅ ድሪዎች ከቀለበቶቹ ጋር እንዲያያዙ አደረጉ፤ 18ሌሎቹንም የሁለቱን ድሪዎች ጫፎች ከሁለቱ ፈርጦች ጋር እንዲገናኙ አደረጉ፤ በዚህም ዐይነት በትከሻ ላይ በሚወርዱት በኤፉድ ማንገቻ ጥብጣቦች ፊት ለፊት እንዲያያዙ አደረጉ። 19በተጨማሪም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተው በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው የደረት ኪስ ሁለት የውስጥ ጫፎች ላይ አደረጉአቸው። 20ቀጥሎም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተው በትከሻ ላይ በፊት በኩል ከሚወርዱት ከሁለቱ የኤፉዱ ጥብጣቦች ጋር ከታች በኩል አያያዙአቸው፤ እነርሱም የተያያዙት በብልኀት ከተጠለፈው ቀበቶ በላይ ከመጋጠሚያው አጠገብ ነበር። 21እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በደረት ኪሱ ላይ ያሉትን ቀለበቶች ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ክር አሠሩ፤ በዚህ ዐይነት የደረት ኪሱ ከቀበቶው በላይ ስለሚውል በቀላሉ የማይፈታ ጥብቅ ነበር።
የቀሩት የካህናት ልብሶች አሠራር
(ዘፀ. 28፥31-43)
22የኤፉዱ መደረቢያ ቀሚስ የተሠራው ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ከፈይ ነበር፤ 23የቀሚሱም ማጥለቂያ አንገትጌ እንዳይተረተር ታጥፎ ዙሪያውን የተዘመዘመ ነበር፤ 24በልብሱ ግርጌ ከሰማያዊ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከጥሩ በፍታ የተጠለፈ የሮማን ፍሬን የመሰለ ጥልፍ ሠሩ። 25ከጥሩ ወርቅም መርገፎችን ሠሩ፤ መርገፎችም በልብሱ ግርጌ ዙሪያ ባለው እንደ ሮማን ፍሬ በሚመስለው ጥልፍ መካከል አስቀመጡአቸው። 26እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት መርገፎቹ የሮማን ፍሬ፥ በልብሱ ግርጌ ዙሪያ አከታትለው አደረጉ።
27ለአሮንና ለልጆቹ የሚከተሉትን ልብሶች አዘጋጁ፤ ሸማኔ ከሠራው ከጥሩ በፍታ ሸሚዞችን፥ 28የራስ መጠምጠሚያዎችን፥ ቆቦችንና ሱሪዎችን፥ 29መታጠቂያውንም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠርተው እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በጥልፍ ጥበብ አስጌጡት። 30የተቀደሰውንም የአክሊል ምልክት ከንጹሕ ወርቅ ሠርተው “ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ” የሚል ቃል እንደ ማኅተም ቀረጹበት። 31እርሱንም እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከመጠምጠሚያው ፊት በሰማያዊ ክር አሰሩት።
የሥራው ሁሉ ፍጻሜ
(ዘፀ. 35፥10-19)
32በመጨረሻም የመገናኛው ድንኳን አሠራር በሙሉ ተፈጸመ፤ እስራኤላውያን ሁሉን ነገር እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት አደረጉ፤ 33ከዚህ በኋላ የሚከተሉትን ዕቃዎች ሁሉ ወደ ሙሴ አመጡአቸው፤ ድንኳኑንና የመገልገያ ዕቃዎቹን ሁሉ እነርሱም፦ ኩላቦቹ፥ ተራዳዎቹ መወርወሪያዎቹ፥ ምሰሶዎቹና የሚቆሙባቸው እግሮች፥ 34ከአውራ በግ ቆዳ ተሠርቶ ቀይ ቀለም የተነከረው መደረቢያ፥ ከለፋ ቆዳ የተሠራው መደረቢያ፥ ለመከለያ የተሠራው መጋረጃ፥ 35የድንጋይ ጽላቶቹ ያሉበት የቃል ኪዳኑ ታቦት፥ መሎጊያዎቹና የስርየት መክደኛው፥ 36ገበታውና የመገልገያ ዕቃዎቹ በሙሉ፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው የተቀደሰው ኅብስት፥ 37ከንጹሕ ወርቅ የተሠራው መቅረዝ፥ የተደረደሩት መብራቶቹና መገልገያ ዕቃዎቹ፥ ለመብራቶቹ የሚሆነው ዘይት፥ 38ከወርቅ የተሠራው መሠዊያ፥ የቅባቱ ዘይት፥ ጣፋጭ ሽታ ያለው ዕጣን፥ ለድንኳኑ ደጃፍ የተሠራለት መጋረጃ፥ 39ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ከነሐስ ከተሠራው መከላከያው ጋር፥ መሎጊያዎቹና የእርሱ መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ የመታጠቢያው ሳሕንና ማስቀመጫው፥ 40ለመገናኛው ድንኳን መግቢያ የሚሆኑት መጋረጃዎች፥ ምሰሶዎቹና የሚቆሙባቸው እግሮች፥ ለአደባባዩ መግቢያ የተሠራው መጋረጃና አውታሮቹ፥ ድንኳኑ የሚተከልባቸው ካስማዎች፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚገኙ የመገልገያ ዕቃዎች፥ 41ካህኑ አሮንና ልጆቹ በተቀደሰው ስፍራ በክህነት ሲያገለግሉ የሚለብሱአቸው የተቀደሱና ውብ የሆኑ የክህነት አልባሳት ናቸው። 42እስራኤላውያን ሥራውን ሁሉ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሠሩ፤ 43ሙሴም ሁሉን ነገር መርምሮ ልክ እግዚአብሔር ባለው መሠረት መሥራታቸውን አረጋገጠ፤ ስለዚህም ሙሴ ባረካቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 39: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997