የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 37

37
የቃል ኪዳኑ ታቦት አሠራር
(ዘፀ. 25፥10-22)
1ባጽልኤልም ከግራር እንጨት የቃል ኪዳኑን ታቦት ሠራ፤ ርዝመቱ መቶ ዐሥር ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑ ስፋት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱም ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ነበር። 2ውስጡንም ውጪውንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገለት፤ 3ለመሸከሚያ የሚያገለግሉ አራት የወርቅ ቀለበቶችም አደረገለት፤ እነርሱንም በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች በሌላውም ወገን ሁለት ቀለበቶች በማድረግ በአራቱ እግሮች ላይ አኖራቸው፤ 4መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። 5በታቦቱ ጐንና ጐን ላይ በተሠሩትም ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው። 6ርዝመቱ መቶ ዐሥር ሳንቲ ሜትር ስፋቱም ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር የሆነ የስርየት መክደኛ ከንጹሕ ወርቅ ሠራ፤ 7ክንፍ ያላቸውንም ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሠርቶ፥ 8በመክደኛው ላይ አንዱን በአንድ በኩል፥ ሁለተኛውንም በሌላ በኩል አደረገው፤ ከመክደኛውም ጋር አንድ ወጥ አድርጎ ሠራቸው። 9ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ዘርግተው መክደኛውን በመሸፈን እርስ በርስ እንዲተያዩ አደረገ።
የተቀደሰው ኅብስት ማኖሪያ ጠረጴዛ አሠራር
(ዘፀ. 25፥23-30)
10ርዝመቱ ሰማኒያ ስምንት ሳንቲ ሜትር የጐኑ ስፋት አርባ አራት ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱም ስድሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር የሚሆን ጠረጴዛ ከግራር እንጨት ሠራ። 11በንጹሕም ወርቅ ለብጦ፥ በዙሪያው የወርቅ ክፈፍ አደረገለት። 12ደግሞም በዙሪያው ሰባ አምስት ሚሊ ሜትር ስፋት ያለው ጠርዝና በጠርዙም ዙሪያ የወርቅ ክፈፍ አደረገለት። 13አራት የወርቅ ቀለበቶች ሠርቶ አራቱ እግሮቹ በተተከሉበት አራት ማእዘኖች ላይ አደረገ። 14ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉ የመሎጊያ ማስገቢያዎቹ ቀለበቶችም በክፈፉ አጠገብ ነበሩ። 15መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። 16በጠረጴዛው ላይ የሚቀመጡ ልዩ ልዩ የመገልገያ ዕቃዎችን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ፤ ይኸውም፦ የዕጣን ማስቀመጫ ዝርግ ሳሕኖችንና ወጭቶችን፥ ጭልፋዎችን ለወይን ጠጅ መቅጃ የሚሆኑ ማንቈርቈሪያዎችንና ጐድጓዳ ሣሕኖችን ሠራ።
የመቅረዙ አሠራር
(ዘፀ. 25፥31-40)
17መቅረዙንም ከንጹሕ ወርቅ ሠራ፤ ማቆሚያውንና ዘንጉንም ከተቀጠቀጠ ወርቅ አበጀ፤ ለጌጥ የሚሆኑትንም የአበባዎች ቅርጽ ከነእንቡጣቸውና ከነቀንበጣቸው አንድ ወጥ አድርጎ ሠራቸው።
18በአንድ በኩል ሦስት፥ በሌላ በኩል ሦስት በመሆን ከጐኖቹ ስድስት ቅርንጫፎች እንዲወጡ አደረገ። 19ስድስቱም ቅርንጫፎች እያንዳንዱ እንቡጥና ቀንበጥ ያላቸውን የለውዝ አበባዎችን የሚመስሉ ሦስት ሦስት ጌጠኛ የአበባ ወርድ ተስለውበት ነበር። 20የመቅረዙም ዘንግ እንቡጥና ቀንበጥ ያላቸውን የለውዝ አበባዎችን የሚመስሉ አራት የጌጠኛ አበባ ወርዶች ተስለውበት ነበር። 21ከሦስቱም ጥንድ ቅርንጫፎች በእያንዳንዱ ጥንድ ሥር አንድ እንቡጥ ተስሎ ነበር፤ 22እንቡጦቹ ቅርንጫፎቹና መቅረዙ ከተቀጠቀጠ ወርቅ አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። 23ለመቅረዙም ሰባት መብራቶችን፥ መኰስተሪያዎችንና የኲስታሪ ማኖሪያዎችን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ። 24መቅረዙንና የእርሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ለመሥራት የፈጀበት የወርቅ መጠን ሠላሳ አምስት ኪሎ ግራም ነበር።
የዕጣን መሠዊያው አሠራር
(ዘፀ. 30፥1-5)
25ርዝመቱ አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑ ስፋት አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር ቁመቱም ዘጠና ሳንቲ ሜትር የሆነ አራት ማእዘን የዕጣን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ በአራቱም ማእዘን ያሉት ጒጦቹ ከእርሱ ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። 26ጫፉን፥ አራት ጐኖቹንና ጒጦቹን ሁሉ በንጹሕ ወርቅ ለበጠ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አበጀለት። 27ከክፈፉም ሥር ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን አደረገ፤ በሁለቱም ጐን ግራና ቀኝ አኖራቸው፤ እነርሱም የዕጣን መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉ መሎጊያዎች የሚሾልኩባቸው ነበሩ። 28መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።
የቅባቱ ዘይትና የዕጣኑ አዘገጃጀት
(ዘፀ. 30፥22-38)
29የተቀደሰውን የቅባት ዘይትና መልካም መዓዛ ያለውንም ጥሩ ዕጣን እንደ ሽቶ ቀላቅሎ ሠራ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ