የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 33:7-23

ኦሪት ዘጸአት 33:7-23 አማ05

የእስራኤል ሕዝብ በሰፈሩበት ቦታ ሁሉ ሙሴ ድንኳኑን ከሰፈሩ ራቅ ባለ ቦታ ይተክለው ነበር፤ እርሱም “ድንኳን” ተብሎ ተጠራ፤ እግዚአብሔርን መጠየቅ የሚፈልግ ሁሉ ወደዚያ ይሄድ ነበር። ሙሴ ወደዚያ በሄደ ቊጥር ሕዝቡ በየድንኳናቸው ደጃፍ ቆመው ሙሴ ወደ ድንኳን እስኪገባ ድረስ ይመለከቱታል። ሙሴም ወደዚያ ከገባ በኋላ የደመናው ዐምድ ወርዶ በድንኳኑ ደጃፍ ይቆማል፤ እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ሆኖ ሙሴን ያነጋግረው ነበር። ሕዝቡ የደመናውን ዐምድ በድንኳኑ ደጃፍ ሲያዩ በየድንኳናቸው ደጃፍ ተንበርክከው ይሰግዱ ነበር። ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር እግዚአብሔር ሙሴን ፊት ለፊት ያነጋግረው ነበር፤ ከዚያም በኋላ ሙሴ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል፤ የእርሱ ረዳት የነበረው ወጣት የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር። ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “ይህን ሕዝብ ወደዚያች ምድር መርቼ እንድወስድ አዝዘኸኛል፤ ነገር ግን ከእኔ ጋር ማንን እንደምትልክ አልነገርከኝም፤ እኔን እንደምታውቀኝና በእኔም ደስ እንደሚልህ ገልጠህልኛል፤ አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ ዐውቅ ዘንድ እንዳገለግልህና አንተን በማስደሰት እንድቀጥል እባክህ መንገድህን አሳየኝ፤ ይህም ሕዝብ ሕዝብህ እንደ ሆነ ተመልከት።” እግዚአብሔርም “እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ ሰላምም እሰጥሃለሁ።” አሳርፍህማለሁ አለው። ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከእኛ ጋር የማትወጣ ከሆንክ፥ እኛንም ከዚህ ስፍራ አታውጣን፤ ከእኛ ጋር የማትወጣ ከሆነ በሕዝብህም ሆነ በእኔና በሕዝብህ ደስ መሰኘትህን ሰዎች ሁሉ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? እኛን በምድር ላይ ካሉት ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየ የሚያደርገን የአንተ ከእኔና ከሕዝብህ ጋር መሆን አይደለምን?” እግዚአብሔርም ሙሴን “እኔ አንተን በሚገባ በትክክል ስለማውቅህና በአንተም ደስ ስለምሰኝ የምትለውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለው። ሙሴም እግዚአብሔርን “እባክህን ክብርህን አሳየኝ” አለው። እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ደግነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ስሜን በፊትህ ዐውጃለሁ፤ የምምረውን እምራለሁ፤ የምራራለትንም እራራለታለሁ፤ ፊቴን አይቶ ለመኖር የሚችል ሰው ስለሌለ ፊቴን ለማየት አትችልም። ነገር ግን እዚህ በአጠገቤ በአለት ላይ የምትቆምበት ስፍራ አለ። የእኔ ክብር በዚያ ሲያልፍ በአለቱ ስንጣቂ አቈይሃለሁ፤ እስካልፍ ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ፤ ከዚያም በኋላ እጄን አነሣለሁ፤ አንተም ፊቴን ሳይሆን ጀርባዬን ታያለህ።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}