በዚያን ጊዜ ከሌዊ ነገድ የሆነ አንድ ሰው አንዲት ሌዋዊት ሴት አገባ፤ እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ሕፃኑ መልከ መልካም መሆኑን አይታ ሦስት ወር ሸሸገችው። ሆኖም ከዚያ በላይ ልትሸሽገው አለመቻልዋን በተረዳች ጊዜ፥ በሣጥን መልክ ከደንገል የተሠራ ቅርጫት አዘጋጀች፤ ውሃም እንዳያስገባ በቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አስገብታ ቅርጫቱን በወንዝ ዳር በሚገኝ ቀጤማ መካከል አስቀመጠችው። የሕፃኑም እኅት የሚደርስበትን ነገር ለማየት ራቅ ብላ ትጠባበቀው ነበር። በዚህ ጊዜ የንጉሡ ሴት ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ሴቶች አገልጋዮችዋም በወንዙ ዳር ይሄዱ ነበር፤ እርስዋም በቀጤማ መካከል የተቀመጠ አንድ ቅርጫት አየች፤ አገልጋይዋንም ልካ አስመጣችው። በከፈተችውም ጊዜ አንድ ሕፃን በውስጡ አገኘች፤ ሕፃኑም ያለቅስ ስለ ነበር አዘነችለትና “ይህ ከዕብራውያን ሕፃናት አንዱ ነው” አለች። በዚያን ጊዜ የሕፃኑ እኅት የንጉሡን ልጅ “ይህን ሕፃን እያጠባች የምታሳድግልሽ ከዕብራውያን ሴቶች አንዲት ሞግዚት ልጥራልሽን?” ስትል ጠየቀቻት። “አዎ፥ ሄደሽ ጥሪልኝ” ስላለቻት ልጅቱ ሄደች፤ የሕፃኑንም እናት ጠርታ አመጣች። የንጉሡ ልጅም ሴትዮይቱን “ይህን ሕፃን ወስደሽ እያጠባሽ አሳድጊልኝ፤ ደመወዝሽንም እከፍልሻለሁ” አለቻት፤ ስለዚህ ሴቲቱ ሕፃኑን ወስዳ ታጠባው ጀመር። ሕፃኑም ባደገ ጊዜ ወደ ንጉሡ ልጅ አመጣችው፤ የእርስዋም ልጅ ተባለ። እርስዋም “ከውሃ ያወጣሁት ስለ ሆነ ስሙ ሙሴ ተብሎ ይጠራ” አለች። ሙሴ ባደገ ጊዜ ወገኖቹን ለመጐብኘት ሄደ፤ ከባድ ሥራ መሥራታቸውን ተመለከተ፤ እንዲያውም አንድ ግብጻዊ ከወገኖቹ አንዱ የሆነውን ዕብራዊ ሲደበድብ አየ። ሙሴ ዙሪያውን ተመልክቶ ማንም እንደማያየው ከተረዳ በኋላ ግብጻዊውን ገድሎ በአሸዋ ውስጥ ደበቀው። በማግስቱም ወደዚያው ስፍራ ተመልሶ ሲሄድ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አየ፤ በደል የሠራውንም ሰው ተመልክቶ “ወገንህ የሆነውን ዕብራዊ ለምን ትመታዋለህ?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም “አንተን በእኛ ላይ ገዢና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ወይስ ያንን ግብጻዊ እንደ ገደልክ እኔንም መግደል ትፈልጋለህን?” አለው፤ ሙሴም እጅግ ፈርቶ “ያደረግኹት ነገር ታውቋል ማለት ነው” ብሎ አሰበ።
ኦሪት ዘጸአት 2 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 2:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos