እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ እኔ ለሁላችሁም የሚበቃ ምግብ ከሰማይ ላዘንብላችሁ ነው፤ ሕዝቡ በየዕለቱ ወጥተው ለዚያው ቀን የሚበቃቸውን ምግብ ይሰብስቡ፤ በዚህ ዐይነት እኔ የምሰጣቸውን መመሪያ ይጠብቁ እንደ ሆነ እፈትናቸዋለሁ። በስድስተኛው ቀን ግን፥ ከሌሎቹ ዕለቶች በአንዱ ቀን የሚሰበስቡትን እጥፍ ሰብስበው ያዘጋጁ።” ስለዚህ ሙሴና አሮን ለመላው የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አሉ፦ “ከግብጽ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር መሆኑን በዛሬይቱ ምሽት ታውቃላችሁ፤ በማለዳ የእግዚአብሔርን ክብር ታያላችሁ፤ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ሰምቶአል፤ በእኛ ላይ የምታጒረመርሙት እኛ ማን ነን?” ከዚህም በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፦ “በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ስለ ሰማ በማታ የምትበሉትን ሥጋና በማለዳ ደግሞ የፈለጋችሁትን ያኽል እንጀራ የሚሰጣችሁ እግዚአብሔር ነው፤ እኛ ምንድን ነን? በእኛ ላይ ስታጒረመርሙ በእግዚአብሔር ላይ ማጒረምረማችሁ ነው።” ሙሴ አሮንን፦ “እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ስለ ሰማ፥ መላው የእስራኤል ማኅበር መጥታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቁሙ ብለህ ንገራቸው” አለው። አሮንም ለመላው ማኅበር በተናገረ ጊዜ ፊታቸውን ወደ በረሓው አዞሩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር በደመና ተገለጠ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያን በእኔ ላይ ማጒረምረማቸውን ሰምቼአለሁ፤ ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በዛሬው ምሽት ፀሐይ ከመጥለቅዋ በፊት ምግብ የሚሆናችሁን ሥጋ ታገኛላችሁ፤ በማለዳም የምትፈልጉትን ያኽል እንጀራ ታገኛላችሁ፤ በዚያን ጊዜም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ።’ ” በምሽትም ብዙ ድርጭቶች እየበረሩ መጥተው ሰፈሩን ሸፈኑት፤ በማለዳ ደግሞ በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ነበረ፤ ጤዛውም ከተነነ በኋላ ደቃቅና ስስ የሆነ ነገር በበረሓማው ምድር ላይ ታየ፤ እርሱም በምድር ላይ ያረፈ ዐመዳይ ይመስል ነበር። እስራኤላውያን ባዩት ጊዜ ምን እንደ ሆነ ባለማወቃቸው “ይህ ነገር ምንድን ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ይህ እንድትበሉት እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው፤ ከእናንተ እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያኽል ብቻ እንዲሰበስብ እግዚአብሔር አዞአል፤ ስለዚህ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አንድ ኪሎ ተኩል ይውሰድ።” እስራኤላውያንም እንደዚሁ አደረጉ፤ አንዳንዶቹ ብዙ አንዳንዶቹ ጥቂት ሰበሰቡ፤ በሰፈሩትም ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አላነሰበትም፤ እያንዳንዱ የሰበሰበው ልክ የሚበቃውን ያኽል ነበር። ሙሴም “ማንም ለዕለት ከሚያስፈልገው አስበልጦ ለነገ ማስተረፍ የለበትም” አለ። አንዳንዶቹ የሙሴን ቃል ባለመስማት ለዕለቱ ከሰበሰቡት ከፍለው አሳደሩ፤ በማግስቱም ጠዋት ተልቶ ተገኘ፤ በስብሶም ሸተተ፤ ሙሴም እጅግ ተቈጣቸው።
ኦሪት ዘጸአት 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 16:4-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች