ኦሪት ዘጸአት 1:15-22
ኦሪት ዘጸአት 1:15-22 አማ05
ከዚህ በኋላ የግብጽ ንጉሥ የዕብራውያን ሴቶችን የሚረዱ ጺጳራና ፉሐ ተብለው የሚጠሩትን ሁለት አዋላጆች እንዲህ አላቸው፤ “የዕብራውያንን ሴቶች በምታዋልዱበት ጊዜ የሚወለደው ሕፃን ወንድ ከሆነ ወዲያውኑ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት እንድትኖር ተዉአት”። አዋላጆቹ ግን እግዚአብሔርን በመፍራት የግብጽ ንጉሥ እንዳዘዛቸው አላደረጉም፤ ወንዶችንም ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ተዉአቸው። ከዚህ በኋላ የግብጽ ንጉሥ አዋላጆቹን አስጠርቶ “ወንዶች ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ያደረጋችኹበት ምክንያት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብጻውያን ሴቶች አይደሉም፤ እነርሱ ብርቱዎች ስለ ሆኑ አዋላጆች ወደ እነርሱ ገና ከመምጣታቸው በፊት ያለምንም ችግር ይወልዳሉ” ሲሉ መለሱለት። አዋላጆቹ እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ እግዚአብሔርም ለእነርሱ መልካም ነገር አደረገላቸው፤ ለያንዳንዳቸውም ቤተሰብ ሰጣቸው፤ በዚህም ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ በቊጥር እየበዙና ብርቱዎችም እየሆኑ ሄዱ። ከዚህም በኋላ ንጉሡ “ከዕብራውያን የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ እያነሣችሁ ዓባይ ወንዝ ውስጥ ጣሉ፤ ሴቶች ልጆች ግን በሕይወት ይኑሩ” ሲል ለሕዝቡ ጥብቅ ትእዛዝ አስተላለፈ።

