መጽሐፈ አስቴር 8
8
አይሁድ ጠላቶቻቸውን መልሰው እንዲወጉ የተነገራቸው መሆኑ
1ንጉሥ አርጤክስስ የአይሁድ ጠላት የነበረውን የሃማንን ሀብት በሙሉ በዚያኑ ዕለት ለአስቴር ሰጣት፤ አስቴርም፥ መርዶክዮስ ለእርስዋ የቅርብ ዘመድ መሆኑን ለንጉሡ ነገረችው፤ መርዶክዮስም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ንጉሡ ፊት መቅረብ ተፈቀደለት፤ 2ንጉሡም የራሱ ማኅተም ያለበትን፥ ከሃማን ጣት ወልቆ እንዲመለስ የተደረገውን ቀለበት ለመርዶክዮስ ሰጠው፤ አስቴርም መርዶክዮስን በሃማን ሀብትና ንብረት ላይ ኀላፊ አድርጋ ሾመችው።
3ከዚህም በኋላ አስቴር በንጉሡ እግር ላይ ወድቃ በማልቀስ እንደገና አቤቱታዋን አቀረበች፤ የአጋግ ዘር የሆነው ሃማን በአይሁድ ላይ የቋጠረውን ክፉ ሤራ ለማቆም አንድ ነገር ያደርግ ዘንድ ለመነችው። 4ንጉሡም የወርቁን በትር ዘረጋላት፤ እርስዋም ተነሥታ በፊቱ በመቆም እንዲህ አለች፤ 5“የግርማዊነትዎ መልካም ፈቃድ ቢሆንና ስለ እኔም የሚያስብልኝ ከሆነ፥ እንዲሁም ጉዳዩ በእርስዎ ፊት ትክክል ሆኖ ከተገኘ፥ በንጉሠ ነገሥት ግዛትዎ ሁሉ ውስጥ የሚገኙ አይሁድ ሁሉ ይደመሰሱ ዘንድ የአጋግ ዘር የነበረው የሃመዳታ ልጅ ሃማን ሰጥቶት የነበረውን ትእዛዝ ሁሉ የሚሽር ዐዋጅ እንዲያስተላልፉልኝ እለምንሃለሁ። 6ይህ ሁሉ ጥፋት በሕዝቤ ላይ ሲደርስና የገዛ ዘመዶቼም ሲገደሉ እንዴት መታገሥ እችላለሁ?”
7ከዚህም በኋላ ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ ሃማን በአይሁድ ላይ ስለ ፈጸመው ሤራ በእንጨት ላይ እንዳሰቀልኩትና ሀብቱንም ሁሉ ለአስቴር እንደ ሰጠሁ የሚታወስ ነው፤ 8ይሁን እንጂ የቤተ መንግሥቱ ማኅተም ያለበትና በንጉሡ ስም የተላለፈ ዐዋጅ ሊለወጥ አይችልም፤ ሆኖም እናንተ በበኩላችሁ የፈለጋችሁትን ነገር ለአይሁድ ጻፉላቸው፤ በእኔም ስም ከጻፋችሁ በኋላ የቤተ መንግሥቱን ማኅተም አትሙበት።”
9ይህም የሆነው ሲዋን ተብሎ የሚጠራው ሦስተኛ ወር በገባ በሃያ ሦስተኛው ቀን ነበር፤ መርዶክዮስ የንጉሡን ጸሐፊዎች ሁሉ ጠርቶ ለአይሁድ፥ ከሕንድ እስከ ኢትዮጵያ ያሉትን መቶ ኻያ ሰባት አገሮች ለሚያስተዳድሩ አገረ ገዢዎችና ሌሎችም ባለሥልጣኖች የሚላኩ ደብዳቤዎችን አስጻፈ፤ ደብዳቤዎቹም በእያንዳንዱ አገር ቋንቋና የአጻጻፍ ሥርዓት እንዲሁም በአይሁድ ቋንቋና የአጻጻፍ ሥርዓት ተከትለው እንዲጻፉ ተደረገ። 10መርዶክዮስ ደብዳቤዎቹን ሁሉ በንጉሥ አርጤክስስ ስም አስጽፎ የቤተ መንግሥቱን ማኅተም አተመባቸው፤ ደብዳቤዎቹም በቤተ መንግሥቱ ጋጥ በተቀለቡ ፈጣን ፈረሶች በሚጋልቡ ጋላቢዎች እጅ እንዲላኩ አደረገ።
11የንጉሡም ዐዋጅ አይሁድ በሚኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ተሰባስበው ራሳቸውን ለመከላከል እንዲደራጁ መብት ይሰጣቸዋል፤ ይኸውም ከየትኛውም ወገንና አገር ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ለማጥቃት የሚነሣውን ማንኛውንም የታጠቀ ኀይል ለማጥፋት፥ ለመግደልና ለመደምሰስ፥ እንዲሁም የጠላቶቻቸውን ሀብትና ንብረት ለመማረክና ለመውሰድ መብት ይሰጣቸዋል። 12ይህም ንጉሣዊ ትእዛዝ አዳር ተብሎ የሚጠራው ዐሥራ ሁለተኛ ወር በገባ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን፥ ማለትም አይሁድ እንዲገደሉ በታቀደበት ዕለት በመላው የፋርስ የንጉሠ ነገሥት ግዛት ሁሉ ሥራ ላይ እንዲውል ተወሰነ። 13ትእዛዙም በየሀገሩ እንደ ሕግ ሆኖ እንዲታወጅና ማንኛውም ሕዝብ እንዲገነዘበው ሆነ፤ በዚህ ዐይነት አይሁድ ያ ዕለት በሚደርስበት ጊዜ በጠላቶቻቸው ላይ የበቀል እርምጃ መውሰድ ይችሉ ዘንድ ሁኔታው ተመቻቸላቸው። 14ፈረሰኞቹም በንጉሡ ትእዛዝ በቤተ መንግሥት ፈረሶች ላይ ተቀምጠው በፍጥነት ጋለቡ፤ ይኸው ንጉሣዊ ትእዛዝ የመናገሻ ከተማ በሆነችው በሱሳም በይፋ ለሕዝብ እንዲነገር ተደረገ።
15መርዶክዮስም ሰማያዊና ነጭ ልብሰ መንግሥት ለብሶ፥ ሐምራዊ ካባ ደርቦና ውብ የሆነ የወርቅ አክሊል ደፍቶ ከቤተ መንግሥት ብቅ አለ፤ በሱሳም ከተማ የሆታና የእልልታ ድምፅ አስተጋባ። 16ይህም ሁኔታ ለአይሁድ ተድላና ደስታ፥ ሐሴትና ክብር ነበር። 17በየትኛውም አገርና በማንኛይቱም ከተማ የንጉሡ ዐዋጅ በተነበበበት ስፍራ ሁሉ በአይሁድ ዘንድ ተድላና ደስታ ሆነ፤ በዚሁ ምክንያት አይሁድን ከመፍራት የተነሣ ከሌሎች አሕዛብ ወገኖች ብዙዎቹ የአይሁድን ሃይማኖት ተቀበሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ አስቴር 8: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997