ስለዚህም ንጉሡና ሃማን ለሁለተኛ ጊዜ ከአስቴር ጋር ለመጋበዝ አብረው ሄዱ፤ የወይን ጠጅ በመጠጣትም ላይ ሳሉ ንጉሡ “አስቴር ሆይ! ምን እንደምትፈልጊ ንገሪኝ፤ የፈለግሺውን ነገር ሁሉ እፈጽምልሻለሁ፤ የመንግሥቴን እኩሌታ እንኳ ቢሆን እሰጥሻለሁ” ሲል እንደገና ጠየቃት። አስቴርም “ንጉሥ ሆይ! በፊትዎ ሞገስ አግኝቼ ከሆነና በትሕትና የማቀርብልዎትን ጥያቄ ሊቀበሉኝ መልካም ፈቃድዎ ከሆነ፥ የእኔ ፍላጎት እኔም ሆንኩ ወገኖቼ በሕይወት መኖር እንድንችል ነው፤ እነሆ እኔና ወገኖቼ ለባርነት መሸጥ አንሶን ለመገደልና ለመደምሰስ ቀርበናል፤ ለባርነት ከመሸጥ የከፋ ነገር ባይደርስብን ኖሮ፥ ዝም ባልኩና እርስዎን ለማስቸገር ባልደፈርኩ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ ልንጠፋና ከምድር ገጽ ልንደመሰስ ተፈርዶብናል!” ስትል መለሰችለት። ከዚህም በኋላ ንጉሥ አርጤክስስ “ይህን ለማድረግ የደፈረ ማን ነው? ለመሆኑ ይህ ሰው የት ይገኛል?” ሲል ንግሥት አስቴርን ጠየቃት። አስቴርም “ጠላታችንና ሞት የፈረደብንማ ሃማን የተባለው ይህ ክፉ ሰው ነው!” አለችው። ሃማንም እጅግ በመደንገጥ አንዴ ወደ ንጉሡ፥ አንዴ ወደ ንግሥቲቱ ይመለከት ነበር፤ ንጉሡም እጅግ ተቈጣና ግብዣውን ትቶ በመነሣት ከነበረበት ክፍል ወጥቶ ወደ ቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ሄደ፤ ንጉሡ በዚህ ጥፋት ሊቀጣው የወሰነ መሆኑን ሃማን ተገንዝቦ ስለ ነበር ሕይወቱን ታተርፍለት ዘንድ ንግሥት አስቴርን ለመማጠን ወደ ኋላ ቀረ። ምሕረትም ለመለመን አስቦ ንግሥት አስቴር በተቀመጠችበት ድንክ አልጋ ላይ በግንባሩ ተደፋ፤ ንጉሡም ከአትክልቱ ቦታ ተመልሶ ወደ ክፍሉ በገባ ጊዜ ይህን በማየቱ እጅግ ተቈጥቶ “ይህ ሰው በገዛ ቤተ መንግሥቴ ዐይኔ እያየ ንግሥቲቱን ሊደፍር ይፈልጋል እንዴ?” ሲል ጮኸበት። ንጉሡም ገና ይህን እንደ ተናገረ ወዲያውኑ ጃንደረቦቹ የሃማንን ፊት ሸፈኑ። ከእነርሱም አንዱ ሐርቦና የተባለው ጃንደረባ “ንጉሥ ሆይ! ሃማን እኮ ከዚህ ሁሉ አልፎ አንተን ከሞት ያዳነህን መርዶክዮስን በስቅላት ሞት ለመቅጣት አስቦ የተከለው እንጨት በቤቱ ይገኛል፤ የእንጨቱም ርዝመት ኻያ ሁለት ሜትር ነው!” ሲል ተናገረ። ንጉሡም “ሃማንን ወስዳችሁ በዚያ እንጨት ላይ ስቀሉት!” ሲል ትእዛዝ ሰጠ። ስለዚህም ሃማን መርዶክዮስን ለመስቀል ባዘጋጀው እንጨት ላይ ተሰቀለ፤ ከዚያም በኋላ የንጉሡ ቊጣ በረደ።
መጽሐፈ አስቴር 7 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ አስቴር 7:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos